በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ሱሰኝነትና ጾታዊ ግንኙነት" ላይ ያተኮረ ስልጠና ለተማሪዎች ተሰጠ

በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ሱሰኝነትና ጾታዊ ግንኙነት" ላይ ያተኮረ ስልጠና ለተማሪዎች ተሰጠ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ካውንስል "ተስፋ ካውንስሊንግ ማህበር" በዋናው ግቢ ከሚገኙ ሁሉም ኮሌጆች ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና "የወጣትነት ዘመንዎን እንዴት ለመኖር አስበዋል?" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ስልጠና በወግ፣ ግጥምና የህይወት ተሞክሮ ፕሮግራሞች ታጅቦ ግንቦት 20/2016 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስ/ል/ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ መድረኩን ሲከፍቱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀለም ትምህርትን በዋነኛነት የሚቀስሙ ቢሆንም ሁለንተናዊ እድገትን ለመላበስ ተጨማሪ የሕይወት ክህሎቶችና እውቀቶችን ሊገበዩ ይገባል ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ወጣት ተማሪዎች ከእድሜያቸው ጋር በተያያዘ ብዙ ፈተናዎችና መሰናክሎች እንደሚገጥማቸው የሚታወቅ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሳሙኤል ይህንን መሰናክል ለማለፍና ሀገርን የሚያኮራ ዜጋ ለመሆን የእውቀት አድማስንና የባህሪ ለውጥን የሚያመጡ መሰል ስልጠናዎች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናውን የሰጡት ዶ/ር ስዩም አንቶንዮስ በበኩላቸው "የወጣትነት ዘመንዎን እንዴት ለመኖር አስበዋል?" የሚለው ጥያቄ ሁሉም የዚህ ዘመን ወጣቶች ሊጠየቁት የሚገባው ጥያቄ መሆኑን ገልጸው ይህንን በአግባቡ ለመመለስና ፍሬያማ የወጣትነት ጊዜን ለመምራት የወቅቱን ፈተናዎች በአግባቡ መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሱስ ዘርፉና አይነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ የመጣበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ያነሱት ዶ/ር ስዩም አሁን ያለንበት ዘመን የማህበራዊ ሚዲያ ጊዜ በመሆኑ አለም ላይ የሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ በእጃችን ቅርብ ሆነው ስለምናገኛቸው አጠቃቀሙን ካላወቅንበት ተጋላጭነታችንና ተጎጂነታችን ሊያመዝን ይችላል ብለዋል። ተማሪዎች የሱስን አስከፊነት፣ የማህበራዊ ሚዲያ አደገኝነትንና አግባብነት የሌለው ጾታዊ ግንኙነት የሚያመጧቸውን አደገኛ ውጤቶች በመረዳት ዘመናቸውን ከሚበላ ነገር እራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ዶ/ር ስዩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ የአሁን ዘመን ወጣቶች ከቴክኖሎጂ እድገትና ግሎባላይዜሽን ጋር ተያይዞ ፈርጀ ብዙ ፈተና የሚገጥማቸው መሆኑንና ቀደም ሲል ለጆሮ እንግዳ የነበሩ ከጾታዊ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አደገኛ ልምምዶች ተጋላጭ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። ተማሪዎች ከእኛ ባህልና እሴት ያፈነገጡ ልምምዶችን ባለመቀበልና ዘመናዊነት በዚያ የሚለካ አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባቸው የገለጹት ዶ/ር ዙፋን ይህንንኑ እውቀት ወደታች ወርደው ለታናናሾቻቸው ሊያስተምሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት ፕሬዚደንት ተማሪ እሰይ ጴጥሮስ ማህበራዊ ሚዲያ በአግባቡ የማንጠቀመው ከሆነ የማገናዘብና የማመዛዘን አቅማችንን በመቀነስ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርብን ጥናቶች ማረጋገጣቸውን ገልጾ ይህንን መጋፈጥ የሚያስችል ሁለንተናዊ ክህሎት ለማግኘት ስልጠናው በብዙ እንደሚያግዝ ተናግሯል። "ተስፋ ካውንስሊንግ ማህበር" በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተማሪዎች የሚገጥማቸውን የተለያዩ ችግሮች በምክክር በመፍታትና ከሚደርስባቸው የስነ-ልቦና እንዲሁም አካላዊ ጫናዎች መላቀቅ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ረገድ መልካም ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና ይኸውም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተማሪ እሰይ ጨምሮ ገልጿል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et