ከስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች ጋር ስለሚኖረው ትብብር ውይይትና አካላዊ ምልከታ ተካሄደ::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴ/ሽ/ም/ ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በስዊዘርላንድ ኢምባሲ የስዊዘርላንድ ልማት ኮርፖሬሽን ግሎባል ፕሮግራም ሱፐርቫይዘርን የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሮዋቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከስዊስ ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመተባበርና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል::

ም/ፕሬዚደንቱ እንዳሉት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑንና በቅርቡም ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን ጠቁመው የስዊዘርላንድ ኤምባሲና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከበርካታ አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ አጋሮች ጋር ዘርፈ ብዙ የትብብር ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል:: ዶ/ር ታፈሰ አክለውም በዩኒቨርሲቲው እየተካሄዱ ከሚገኙ በርካታ ምርምሮች አንዱ የብላክ ሶልጀር ነፍሳት ላይ የሚደረገው ጥናት ሲሆን ነፍሳቱ ቆሻሻን በምግብነት ተጠቅሞ የሚራባ እና ለዶሮና ለአሳ ምግብነት የሚውል ከመሆኑም ባሻገር እንዲሁም ከነፍሳቱ የሚወገደው አይነ ምድር ለአፈር ማዳበሪያነት የሚውል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልፀው የዚህ መሰሉ የትብብር ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው በዩኒቨርሲቲው በኩል ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የስዊዘርላንድ ልማት ኮርፖሬሽን ግሎባል ፕሮግራም ሱፐርቫይዘር አቶ አምሳሉ አንዳርጌ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ኤሲፒኤ የተባለ ድርጅት ለሚሰራቸው የምርምር ስራዎች ከዚህ በፊት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ኤሲፒኤም ይሄንን የመሰለ የምርምር ውጤት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመስራቱ ሊሳካ በመቻሉ መደሰታቸውን እና በዩኒቨርሲቲው ያለው ተሞክሮ ጠቃሚ በመሆኑ የዚህን መሰል የምርምር ውጤት ለማስተዋወቅ፣ ተደራሽ ለማድረግ፣ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ወደፊትም የገቢ ምንጭ ለማድረግ በጋራ መስራቱ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑበት ተናግረዋል:: ወደፊትም ያሉትን አጋጣሚዎች በመጠቀም መሰል የትብብር ስራዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንደሚቀጥል ሱፐርቫይዘሩ ገልፀዋል፡፡

የኤሲፒኤ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ታደለ ታፈሰ ይሄንን የምርምር ስራ ለመስራት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ሲመርጡ ዋና ተግባሩ የሰው ሃብት ላይና ምርምር ላይ በመሆኑ ለተማሪዎች፣ ባለሙያዎችና በዚህ መስክ መሳተፍ ለሚፈልጉ እንደስልጠና ማዕከል በማገልገል የተግባር ተሞክሮ እንዲደረግበት፣ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው፣ ሌሎች ለመኖ የሚሆኑ ነፍሳት ላይም ምርምር እንዲደረግና ወደፊትም የገቢ ምንጭ እንዲሆን በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የዶክትሬት ዲግሪውን ምርምር በብላክ ሶልጀር ነፍሳት ላይ እያደረገ ያለው መ/ር እዮብ ከፈኒ ምርምሩን እየሰራበት ያለውን የምርምር ማዕከል እና የዓሣ ምርምር ማዕከል የመስክ ጉብኝት ምልከታ ተደርጎ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et