ለሲዳማ ክልል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሳነ መምህራን እና የሴክተሩ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የም/ቴ/ሽ/ም/ ፕ/ጽ/ቤት ስር በሚገኘዉ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት ከሲዳማ ክልል ለተዉጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሳነ-መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና በየደረጃዉ የሚገኙ የትምህርት ሴክተር አመራሮች ከየካቲት 21/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአመራርነት አቅም ማሻሻያ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የምር/ቴ/ሽ/ም/ ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ በመክፈቻዉ ላይ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲዉ ላለፉት 12 ዓመታት በሰብል ምርት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ ማህበራዊ ስራዎች ላይ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰዉ ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለዉ በመገንዘብ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እንደሀገር የተጀመሩ ለዉጦችን በመደገፍ ዩኒቨርሲቲዉ የድርሻዉን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል። ም/ፕሬዚደንቱ ዩኒቨርሲቲዉ በሀገር ደረጃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ሲደረግ አስተባባሪ በመሆን መማሪያ መፅሐፍትን የማዘጋጀት፣ በክልሉ የሚገኙ ት/ቤቶችን አቅም የማጎልበት፣ ሞዴል ት/ት ቤት በመክፈት የነገ የሳይንስ ምሩቃንን ለማፍራት እና አቅም የሌላቸዉ ተማሪዎችን ደግሞ አወዳድሮ በነፃ የማስተማር፣ የSTEM ማዕከል በመክፈት ተማሪዎች የተግባር ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግ እንዲሁም ለመምህራንና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ይህንን መሰል ስልጠና በመስጠት በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
የዕለቱን ስልጠና አስመልከቶም ባለፉት 2 ዓመታት በሲዳማ ክልል የሚገኙ ት/ቤቶች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስፈትነዉ ዝቅተኛ ዉጤት የመጣባቸዉ ት/ቤቶችን በመለየት በየደረጃዉ ለሚገኙ ኃላፊዎች በትምህርት ቤት አመራር ላይ በማሰልጠን ሰልጣኞች ዕዉቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ላይ በመስራት ተማሪዎችን አንፆ ብቁ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ በስልጠናዉ ያገኙትን ግብዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዶ/ር ታፈሰ አሳስበዋል።
በሲዳማ ክልል ት/ቢሮ የፈተናዎች አስተዳደርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አሳምነዉ አዳቶ በበኩላቸዉ የትምህርት ጉዳይ እንደሀገርም የተፈተንበት ሲሆን በሲዳማ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ለታየዉ የተማሪዎች ዉጤት ማሽቆልቆልና ዉድቀት ደግሞ ሁላችንም በክልሉ ያለን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ድርሻችን አለበት በማለት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ያሉትን ክፍተቶች ተረድቶ የዚህ መሰሉን ስልጠና በማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።