የፓናል ወይይት በአድዋ ላይ

አድዋ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል የፓናል ወይይት ተካሄደ።

"የሀገር ግንባታ መሠረታዊያን: አድዋ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የፓናል ዉይይት አካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመክፈቻ ንግግራቸዉ ኢትዮጵያ ረጅም የዘመነ መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም ገና የሀገረ መንግስት ግንባታዋ ያልተጠናቀቀበት ሀገር መሆኗን ጠቁመው ነገር ግን በጋራ ቆመዉ፣ በጋራ ሞተዉ ሃገራቸዉን የታደጉ ኩሩ ዜጎችን ያፈራች፣ በዓለም ላይ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት እና የጥቁር ህዝቦች ድል ምልክት እንደሆነች የአድዋን ድል ማስታወስ በቂ መሆኑን ገልፀዋል።

የመጀመሪያዉ ጥናት አቅራቢ በሕ/ገ/ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ተባባሪ ዲን ዶ/ር ንጉስ በላይ ሲሆኑ ኢትዮጵያ የሰዉ ዘር መገኛ፣ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት፣ ብቸኛ በቀኝ ገዥዎች ያልተገዛችና ነፃነቷን ያስከበረች እንዲሁም ሌሎች በርከት ያሉ ማህበራዊና ኃይማኖታዊ ትሩፋቶች ያሏት ሀገር መሆኗን በመጥቀስ በሌላ በኩል ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በድህነት፣ በፓለቲካ አለመረጋጋትና በአካባቢያዊ ግጭቶች አሳሯን ያየች አሁንም በዚሁ አዙሪት ዉስጥ የምትገኝ ሀገር መሆኗን ገልፀዋል። ዶ/ር ንጉስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለችግሮቿ አንዱ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ያስተዳደሯት መሪዎች ሀገሪቷን ለመገንባት የሄዱበት የሀገር ግንባታ (Nation Building) ጉዞው ከሀገረ መንግስት ግንባታ (State Building) ጉዞ አንፃር ወደኋላ የቀረ መሆኑን በጥናታዊ ፅሁፋቸው ገልፀዋል። የዶ/ር ንጉስ ፅሁፍ "ሃገራዊ እሴቶች" በሚል ርዕስ ላይ ያተኮረ ሲሆን ሀገራችን በህግ ድንጋጌ ጭምር የታገዙ፣ በሀገር በቀል እሴቶች ላይ የተመሰረቱ እና ዘመኑን የሚመጥኑ እሴቶች ጎልብተው ቢሰራባቸው የተረጋጋ ሃገረ መንግስት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ አስረድተዋል::

የኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ ረ/ፕ ዮሴፍ ዋቴ በበኩላቸው "ብሔራዊ ማንነት" በሚል ርዕስ የማንነት ትርጓሜና የምሁራን ዕይታዎችን አብራርተው ህዝቦች የጋራ ማንነትና ኩራት እንዲሰማቸው እንደ አድዋ ድል በዓል ያሉትን ስናከብር ከልዩነት ይልቅ አንድነት ላይ ማትኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

ሌላው የፅሁፍ አቅራቢ የኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ መ/ር አወል አሊ "ብሔራዊ ጥቅም" በሚል ርዕስ የዜጎች ኃላፊነት እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያችን ፉክክር በበዛበት ዓለም ውስጥ ሃገራዊ ጥቅምን ያስጠበቀ እንዲሆን መሰራት በሚገባቸው ሥራዎች ላይ አተኩረዋል::

በፓናል ውይይቱ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤ/ት የዉጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ የሰላም ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚደንትና ም/ፕሬዚደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችዉ የሲዳማ ክልልና ሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በቀረቡት የመወያያ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ጠንካራ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንዲሁም ገንቢ ሃሳቦች ተሰጥቶባቸዉ ዉይይቱ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et