የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 531 ተማሪዎችን አስመረቀ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ18ኛው ዙር 493 ተማሪዎችን በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመርቋል::

በዛሬው ዕለት ኮሌጁ ያስመረቃቸው 391 (145 ሴቶችና 246 ወንዶች የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ) በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 16 ስፔሻሊስት ሀኪሞችና 86 የሁለተኛ ዲግሪ የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ በምረቃው ፕሮግራም ላይ የሲዳማ ብ/ክ/መ/ም/ር/መስተደድርና የት/ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ በየነ በራሳ፣ የሲ/ብ/ክ/መ/ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰብ ተገኝተዋል።

የክብር እንግዳው ክቡር አቶ በየነ በራሳ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለሀገር እድገትና ብልጽግና መሰረት መሆኑን በተለይም ደግሞ የጤና ሳይንስ ትምህርት የሰው ልጆችን ጤና የሚያስጠበቅ በመሆኑ ይህንን ከፍተኛ ትጋት የሚጠይቅ ትምህርት በስኬት በማጠናቀቃችሁ በራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል። የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ በትምህርትና በሆስፒታል አገልግሎቱ ለሲዳማ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች እያደረገ ያለውንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ በበኩላቸው ለዕለቱ ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት ራስ-ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስችለው የሽግግር ጉዞ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው በተመረጡ የትኩረት መስኮችና የልህቀት ማዕከላት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አክለውም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመማር ማስተማር እንዲሁም በምርምር ስራ ስኬታማ ከሆኑ የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች አንዱ መሆኑንና በዘንድሮው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መውጫና የሙያ ፈቃድ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎቹ መካከል 99.5% ያህሉን ማሳለፉ ለዚህ ማሳያ ሆኖ መቅረብ ይችላል ብለዋል።

የኮሌጁ ቺፍ ኤክሴክዩቲቪ ዳይሬክተር ተ/ፕ/ር አለሙ ጣሚሶ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በኮምፕሪሔንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታሉ በዓመት ከ18 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገልግሎቶቹን በሰብ-ስፔሻሊቲ ዘርፍ በማስፋፋት የካንሰር ጨረር ህክምና፣ የፎረንሲክ እና ስነምረዛ አገልግሎቶችን ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የዛሬውን ምረቃ ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ከ60% በላይ የሚሆኑት የማዕረግ ተመራቂ መሆናቸው እና በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ተመራቂዎች ታሪክ ከፍተኛው ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ውጤት መሳካት የለፉ መምህራን፣ ባለሙያዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የኮሌጁና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምስጋና እንደሚገባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያም ከየዲፖርትመንቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛውን ዉጤት 3.95 ያስመዘገበችው ዶ/ር ሶስና ሸለመ የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et