የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻ ማዕከል ሲያሰለጥናቸው ለቆየው ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሥራ ዓለም ላይ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል አልሞ የሚሰራው የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻ ማዕከል ስልጠና ሲሰጣቸው ለነበሩ ተማሪዎች የማጠቃለያና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ መድረክ የካቲት 13/2016 ዓም በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አዘጋጅቷል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍስሀ ጌታቸው ለአንድ ወር ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና አጠናቀው በዕለቱ ሰርተፊኬት ላገኙ ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለው ለዚህ ስልጠና መሳካት ትብብር ያደረጉ የማዕከሉ ሰራተኞችና አጋር ድርጅቶችን በዩኒቨርሲቲውና በራሳቸው ስም አመስግነዋል። ም/ፕሬዚደንቱ ማዕከሉ ለተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ማሻሻያ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዩኒቨርሲቲው እንደሚደግፍና ሰልጣኝ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር ሁለንተናዊ ስብዕናቸው የተገነባና ብቁ ዜጋ ሆነው መውጣት እንዲችሉ የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የማዕከሉ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ክብረት ፍቃዱ በበኩላቸው ማዕከሉ ከተቋቋመ አራት አመት ብቻ የሆነው ቢሆንም በየአመቱ ተመራቂ ተማሪዎች ከተለያዩ ኮሌጆች በመሰብሰብ እውቀት የማስጨበጥና ክህሎት የማስታጠቅ ስልጠና በመስጠት እስካሁን 697 ሰልጣኞችን ማስመረቁን ገልጸዋል። ሰልጣኝ ተማሪዎች ራሳቸውን ማወቅ እንዲችሉ፣ ክህሎታቸውን በመለየት እንዴት ያንን ማሳደግ እንደሚችሉ ብሎም ውጤታማ የስራ አፈላላግ ዘዴዎችን በመጠቀም በቀላሉ የቀጣሪ ድርጅቶች ምርጫ መሆን የሚችሉበትን ልምድ መቅሰማቸውን አቶ ክብረት ተናግረዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ተመራቂ ተማሪ የሆነችው እምነት በየነ በስልጠና ቆይታቸው ጥንካሬና ድክመታቸውን ለይተው በማወቅ፣ የተግባቦትና ተባብሮ የመስራት ችሎታን እንዲሁም ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ልምድን ማዳበር በሚችሉበት ዙሪያ እውቀት መገብየታቸውን ተናግራለች።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ፣ የተ/ቀ/ሣ/ኮ/ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ፣ የማ/ሣ/ስ/ሰ/ኮ/ዲን ፕ/ር ዘለቀ አርፍጮ እና አቶ ንፍታሌም ቢንያም በዕለቱ ተገኝተው የህይወት ልምዳቸውን ለተመራቂ ሰልጣኞች ያጋሩ ሲሆን በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ለሁሉም ሰልጣኞች ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል። በዚህ ፕሮግራም ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የማዕከሉ ሰራተኞች፣ የደረጃ ዶት ኮም ሰራተኞች እና ሰልጣኝ ተማሪዎች ተሳታፊ ነበሩ።