የራስ-ገዝ አደረጃጀት ኮሚቴ ጥናት ሪፖርት

የራስ-ገዝ አደረጃጀት ኮሚቴ ጥናት ሪፖርት ላይ የውይይትና ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር የተቋቋመው 49 አባላት ያሉት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ኮሚቴ የጥናት ውጤት ላይ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ውስጣዊ ግምገማ በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ እየተካሄደ ነው::

የአብይ ኮሚቴው አስተባባሪ ፕ/ር ተስፋዬ አበበ መድረኩን ሲያስተዋውቁ እንደገለፁት ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎችን ይዞ እየሰራ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ቀርቦ የተገመገመው የነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ ላይ ያተኮረ ሲሆን የአሁኑ መድረክ ላይ የሚቀርበው የአፈፃፀም ስትራቴጂክ ዕቅድ መሆኑን አብራርተዋል:: ፕ/ር ተስፋዬ
የግብርና ኮሌጅ እና የወንዶገነት ኮሌጅ የቀድሞ ምሩቃንን ሳይጨምር እስካሁን 108,330 ምሩቃንን ያፈራው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ በጣም ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቁመው ራስ ገዝ ለመሆን ደግሞ የበለጠ ሳቢ ማድረግ ከኛ ይጠበቃል ብለዋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲዎች መንግስት ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ከመሆን ተላቀው በራሳቸው መተዳደር፣ ሀብት ማመንጨት ብሎም ማስተዳደር እንዲችሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ይህንን የራስ-ገዝነት ጉዞ ለማሳለጥ ኮሚቴ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም መንግስት ባስቀመጠው የሁለት አመት የራስገዝነት የሽግግር ጊዜ ውስጥ ራስ ገዝ ሆኖ መውጣት ይችል ዘንድ በኮሚቴው አባላት በተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ላይ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚቆይ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ወደ ትግበራ ለመግባት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ፕሬዚደንቱ ለተሳታፊዎች ይሄ የሽግግር ግዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ ከተቀመጠለት የሁለት ዓመት ግዜ በላይ ጭምር እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ስለሚችል በጥልቀት አይተን ራሳችንን የምናጠናክርበት ስለሆነ በደንብ ገምግመን አስፈላጊ ግብዓት እንድንሰጥ አደራ እላለሁ ብለዋል:: በተጨማሪም ከዚህ ግምገማ በኃላ በየደረጃው ለሚመለከተው የበላይ አካል ቀርቦ አስተያየት የሚሰጥበት እና በየደረጃው ያሉ የአረዳድ ብዥታዎችን ለማጥራት የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ጭምር ተሳትፈው በደንብ እየተረዱ ለሚቀጥለው ውይይት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ዶ/ር አያኖ አሳስበዋል::

በዛሬው ውሎ ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች የስራቸውን ውጤት ያቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በነገው ዕለት እንደሚያቀርቡ ታውቋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et