በEUPE ፕሮጀክት የተሰሩ የምርምር ሥራዎች ላይ ግምገማ ተካሄደ

የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ በEUPE ፕሮጀክት የተሰሩ የምርምር ሥራዎች ውስጣዊ ግምገማ አካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ እና በብሪቲሽ ካውንስል የትብብር ፕሮጀክት (EUPE) ድጋፍ የተሰሩ ጥናቶች ውጤት በዋናው ግቢ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የውስጥ ግምገማ ተደርጎባቸዋል::

የግምገማ መድረኩን የከፈቱት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችንና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን እያበረከተ ያለ ተቋም መሆኑን ጠቁመው በተያዘው በጀት አመት 27 ቴማቲክ (ጭብጥ ተኮር)፣ 70 ዲሲፕሊነሪ እንዲሁም በNORAD የሚደገፉ 31 መካከለኛ እና 35 አነስተኛ ደረጃ ያላቸው የምርምር ፕሮጀክቶች በሂደት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል። ም/ፕሬዚደንቱ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ከተሰጠባቸው የምርምር አቅጣጫዎች መካከል የሰላም ግንባታው ዘርፍ አንዱና ዋነኛው እንደመሆኑ የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ በ(Enabling University Peace Education, EUPE) ፕሮጀክት ስር ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችና ሚናቸው ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን አካሂዶ ለውስጣዊ ግምገማ ማቅረቡ ያስመሰግነዋል ብለዋል።

የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን እና የEUPE ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በጅማና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሲቲ የሰላም ትምህርትን ለማጎልበት ታስቦ የተቋቋመና በእስካሁኑ ቆይታው የተለያዩ ስልጠናዎችንና ምርምሮችን ማከናወኑን አስረድተዋል። ዲኑ በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው መምህራን የተሰሩ ስምንት የሚደርሱ በሲዳማና አከባቢው ማህበረሰብ ባሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንዲሁም ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ስላላቸው ሚና የሚዳስሱ ጥናቶች ቀርበው ውስጣዊ ግምገማ እንደሚካሄድባቸውና በቀጣይም ውጫዊ ግምገማ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የምርምር ውጤታቸውን ካቀረቡ መምህራን አንዱ የሆኑት የህግ ት/ቤት መምህር ይርጋለም ጉርሙ የሲዳማ ህዝብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በሆነው "አፊኒ" ስርዓት ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን ገልጸው ይህ ድንቅ የሆነ ባህላዊ እሴት በሽግግር ፍትህ እና በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሂደት ላይ ሊያደርግ ስለሚችለው አዎንታዊ ሚና ገለጻ መካሄዱን ተናግረዋል። በተጨማሪም "ሀላሌ" የተባለው ስርዓት እውነትን በማፈላለግና ተበዳይን በማድመጥ ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰፍን የሚሄድበት አካሄድ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአለም ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የገለጹት አቶ ይርጋለም መሰል መፍትሔዎች ከዚያው ከማህበረሰቡ እንዲፈልቁ መደረጉ ውጤታማነታቸውን በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et