የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ የዩኒቨርሲቲዉን የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀም ከጥር 25 -26/2016 ዓም በነበረው መደበኛ ስብሰባው ገምግሟል::
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትርና የቦርድ ሰብሳቢ ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በመክፈቻዉ ላይ እንደገለፁት በዚህ ዉይይት በዩኒቨርሲቲው የ2016 ዓ.ም የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፓርት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዉ ያለዉን የኢንተርፕራይዝ ሥራ ሂደት ሪፓርትና መዋቅሩንም በተመለከተ በሚቀርቡ ሰነዶች ላይ ግምገማና ውይይት ከማድረግ ባሻገር የዩኒቨርሲቲዉ የራስ ገዝነት ሂደትንም በጥልቀት እንደሚዳስሱ ገልፀዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ የዩኒቨርሲቲዉን አጠቃላይ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ዩኒቨርሲቲዉ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆንና በቀጣይም ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዉ በተሰጡትና በተለዩት ተቋማው የትኩረት መስኮች አንፃር የተከናወኑ ተግባራትንና አፈፃፀማቸዉን በሰፊዉ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ተቋሙ መደበኛ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ቴ/ሽግግር እንዲሁም የማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎቹ በተጨማሪ 48,782 ተማሪዎችን በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተቀብሎ ማስፈተኑን፣ የዩኒቨርሲቲዉ የአስተዳደር ሰራተኞች መዋቅር ማሻሻያን አጥንቶ በማዘጋጀትና በማፀደቅ የሰራተኞች ምደባ በመመሪያዉ መሰረት እያከናወነ መሆኑን፣ የአረንጓዴ ችግኝ ተከላ እና የአፈር መራቆት መከላከል ላይ በሰፊዉ እየሰራ መሆኑን፣ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት የዩኒቨርሲቲዉን አሁናዊ ቁመና በኮሚቴ አስጠንቶ በሴኔት ማስገምገሙን፣ የተለያዩ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸዉ የምሁራን ዉይይቶች እንዲቀርቡ መደረጉን፣ የተማሪዎች ፋሲሊቲና ዲጅታል ቴክኖሎጂ ስርዓት ዝርጋታ እንዲሻሻሉ መደረጉን፣ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችና ቴክኖሎጂዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ መደረጉን፣ በዩኒቨርሲቲዉ ሞዴል የማህበረሰብ ት/ቤት መከፈቱን፣ ከበርካታ የተለያዩ ተቋማት ጋር ለመስራት ስምምነት መፈራረሙን፣ በርካታ የምርምር ዉጤቶችን በታዋቂ ጆርናሎች ማሳተም መቻሉን፣ ከመንግስት በተገኘ 1.1 ቢሊየን ብር የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት ለማስጀመር ወደስራ መገባቱን፣ 84 የትብብር ፕሮጀክቶች በስራ ላይ መሆናቸዉን በሪፖርታቸዉ ላይ ገልፀዋል።
ፕሬዚደንቱ በሪፖርታቸው የበጀት ዕጥረት፣ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር፣ የግንባታ ድርጅቶች የስራ ፍላጎት መቀነስ፣ የተማሪዎች ቁጥር መቀነስ፣ የምርምር ግብዓቶች ዋጋ መናርና አለመገኘት እንዲሁም የተሽከርካሪ ዕጥረት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸዉን አመላክተዋል።
ቦርዱ በቀረበዉ ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየት እንዲሁም ዉይይትና ግምገማ ያካሄደ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ መዋቅርና አፈፃፀም ላይ ሰፊ ግምገማ አድርጓል:: በሁለተኛው ቀን ውሎ የተለያዩ ካምፓሶች ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ኃላፊዎቹ በአካል ጎብኝተዋል::