ከጥር 8-9/2016 ዓም ሲካሄድ የነበረው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በሁለተኛዉ ቀን ውሎ በኮሌጆችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ዉይይት ተደርጎ በተሳታፊዎች በተነሱ ነጥቦች ላይ ምላሾች ተሰጥተዋል::
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ የሰራተኞች ዉድድርና ድልድል በመመሪያና መስፈርት መሰረት እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይም የሰራተኞች የት/ት እና የስራ ማስረጃዎችን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም ሀሰተኛዉን ከትክክለኛዉ ለመለየት የማጣራት ስራዎች እንደሚጀመር ገልፀዋል።
የም/ቴ/ሽግግር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ ምርምርን በተመለከተ በአብዛኛዉ ኮሌጅ የሚገኙ ተመራማሪዎች የሚሰሩ ምርምሮች በተገቢዉ ሪፖርት እንደማይደረጉ፣ የተሰሩትም ለህትመት እንደማይበቁ፣ ለአለም አቀፍ የምርምር አዉደ ርዕይ የተመደበዉን በጀትም በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በማጠቃለያ ንግግራቸዉ እንደገለፁት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ሲቀርብ ከውጤት አመላካች ቁልፍ መለኪያዎች አንፃር ጭምር የተሟላ መሆን እንዳለበት፣ የበጀት ዕጥረት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የአጠቃቀም ብክነት እየታየ በመሆኑ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ወጪን በመቀነስና የውስጥ ገቢን ማሳደግ ላይ መሰራት እንዳለበት፣ ፈተናና ፈታኞችን በተመለከተ አመዳደብ፣ መረጃ ስርዓትና ተግባቦት ላይ ችግሮች መኖራቸዉን፣ ኮሌጆችና የት/ት ክፍሎች የተማሪዎች ቁጥር እየተመናመነ ጭራሽ እንዳይዘጋ ጥራት ያለዉና ተመራጭ ሆኖ ለመቀጠል በርትተዉ መስራት እንዳለባቸዉ እንዲሁም ሁሉም ኮሌጆች በተልዕኮ ከተሰጣቸዉ ተግባሮች ጋር በተያያዘ ገቢ ማስገኘት ላይ በርትተዉ በመስራት ተቋሙንም መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዉ በቀጣይ የታዩ ክፍተቶች ላይ በትኩረት መስራትና ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል ለተሻለ ዉጤት ወሳኝ መሆናቸውን አስምረውበታል።
በመጨረሻም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ለፕሬዚደንቱና ምክትል ፕሬዚደንቶች በ3D የተሰራ ምስላቸው ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን በኢንስቲቱዩቱ የሚገኙ ሰርቶ ማሳያዎች፣ ቤተ ሙከራዎችና የተደራጁ ክፍሎች ተጎብኝተዉ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።