በ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ግምገማ ማካሄድ ተጀመረ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስተናጋጅነት ከጥር 8-9/2016 ዓም የሚካሄደዉን የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ሲከፍቱ በየዓመቱ የታቀዱ ሥራዎች አፈፃፀም የሚፈተሽበትና የሚገመገምበት ወሳኝ የስራ አካል መሆኑን ጠቁመው በመድረኩ ጠንካራ አፈፃፀሞችን ለማስቀጠል እንዲሁም ደካማ አፈፃፀሞችን ለማረም ዕድል እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ባለፉት ስድስት ወራት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሀገር አቀፍ የመዉጫ ፈተና ላይ ጥሩ ዉጤት በማስመዝገብ እንደሀገር ሁለተኛ መሆኑን፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በሁለት ዙር ተቀብሎ በተሳካ ሁኔታ ማስፈፀሙን እንዲሁም በ2016 ዓ.ም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዲስ ተማሪዎችን ከተቀበሉ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም መሆኑን አዉስተዉ ይሄም በዩኒቨርሲቲው ጥንካሬ፣ አቀባበልና በተማሪዎቹም ተመራጭ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል:: የዩኒቨርሲቲዉን የራስ ገዝነት ሂደት በተመለከተም ጥናት እየተካሄደ እንደሆነና ወደፊትም አደረጃጀትና ስትራቴጂክ ዕቅዶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ እንዲሁም የአስተዳደር ሰራተኞች የመዋቅር ጉዳይ የመጀመሪያው ዙር ዉድድር ተካሂዶ ምደባ የተካሄደ ሲሆን የቀረቡ ቅሬታዎች ከታዩ በኃላ በቀጣይ የሰራተኞች ዉድድርና ምደባ እንደሚካሄድ ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል። መንግስት በተለያዩ ጊዜያት እንደየሁኔታዉ መዋቅሮችን የሚለዋዉጥና የሚያወዳድር መሆኑን መቀበል እንጂ ሰራተኞች ሊያባርር እንደሆነ የሚናፈሰዉ ዉዥንብር ስህተት መሆኑን ፕሬዚደንቱ ገልፀዉ ነገር ግን ይሄ ዉድድር እና ድልድል እስኪያልቅ ሰራተኛዉ ተረጋግቶ ስራዉን መስራት እንደሚገባዉ አሳስበዋል።
በወጣው መርሃግብር መሰረትም የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የአፈፃፀም ሪፖርታቸዉን አቅርበዉ እየተገመገሙና ዉይይት እየተካሄደባቸዉ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ኮሌጆች በወጣላቸዉ ፕሮግራም መሰረት አፈፃፀማቸዉን የሚያቀርቡ ይሆናል።