የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተዘጋጀ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ለገቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ልዩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተዘጋጀ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናዉ ግቢ የኢንክሉሲቭነስ (የአካቶ) ክበብ ከተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬትና ከትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በአካል ጉዳት ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫና በ2016 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው ለገቡ አዲስ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ልዩ ፕሮግራም አዘጋጅቷል።

የዩኒቨርሲቲዉ የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነ ገልፀው ነገር ግን አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ በማህበረሰባችን ዘንድ ያለዉ ግንዛቤ ከፍያለ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞችን ዝቅ አድርጎ የማየትና ተገቢዉን ክብር አለመስጠት የሚስተዋሉ ክፍተቶች መሆናቸዉን ተናግረዋል። ዶ/ር ሳሙኤል አክለዉም ዩኒቨርሲቲዉ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት በመስጠት የአካል ጉዳተኞች ማዕከል አቋቁሞ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን፣ የተለያዩ አገልግሎትና ድጋፎችን እየሰጠና መሰረተ ልማቶችንም ለማሟላት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዉ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ ለገቡ አዲስ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችም እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ከአመለካከት ጀምሮ አንዳንዴ ነገሮችን በጠበቃችሁትና በሚገባችሁ ልክ ሳታገኙ ስትቀሩ ከመከፋትና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ሆደሰፊና ታታሪ በመሆን እስካሁን ይዛችሁ የመጣችሁትን ጥሩ ዉጤት እዚህም ለማስመዝገብ እንድትበረቱ ዩኒቨርሲቲው የተቻለዉን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

የትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ በበኩላቸዉ ብዙዎቻችን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የተለያዩ ጉድለቶች ያሉብን ሲሆን ክፍተትና ጉድለቶቻችን የሚሞሉት ስንተሳሰብና ስንደጋገፍ ነዉ በማለት ክበቡ ፈቃደኛ በሆኑ አባላቶቹ አማካኝነት እያደረገ ላለዉ እንቅስቃሴና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሕግ ትምህርት ቤት ኃላፊና መምህር በሃይሉ እሸቱ እንደዚሁ አካል ጉዳተኞች የማህበረሰቡ አንድ አካል መሆናቸዉን በመጥቀስ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በተመለከተ በአለም አቀፍ ሕጎችና ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች፣ በሀገራችን ሕገ መንግስት፣ ሀገራችን በተቀበለቻቸዉ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችና በዩኒቨርሲቲዉ ሴኔት ሌጅስሌቲቭ የሕግ መሰረቶችና ድጋፍ እንዳሉት ገለፃ አድርገው ነገር ግን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ተግባር ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው ብዙ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et