የፓናል ውይይት መድረክ ተዘጋጀ

የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የፓናል ውይይት መድረክ አዘጋጀ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ "ስነ-ህዝብ እና የህዝብ ብዛትን እንደ ትሩፋት የመጠቀም መነሻዎች"፣ "ወጣቶችና የስራ ገበያ ሁኔታ በኢትዮጵያ"፣ እና "ስደት፣ ፍልሰትና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች" በሚሉ ሦስት ተያያዥ አርዕስት ላይ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ የተመራ የፓናል ውይይት መድረክ አዘጋጅቷል::

ጥር 3/2016 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ ከሲዳማ ክልል እና ከኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን የመጡ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከሚጠበቅባቸው ድርሻዎች አንዱ በሀገሪቱ እየሆኑ ያሉ ነባራዊ ሁነቶችን በምርምሮችና በውይይቶች በማበልጸግ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በዚህ ረገድ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በአሁኑ ሰዓት አሳሳቢ በሆኑት የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የወጣቶች የስራ እድል ሁኔታ እንዲሁም ስደትን በተመለከቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለውን ጥናታዊ ጽሁፍ ለውይይት እንዲቀርብ በማስቻሉ ትልቅ ምስጋና እንደሚገባው ተናግረዋል።

የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕ/ር ዘለቀ አርፍጮ በበኩላቸው ለመድረኩ የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች በስነ ህዝብ: በሶስዮሎጂ እና በጂኦግራፊ የጥናትና ምርምር ዘርፎች የካበተ እውቀትና ተሞክሮ ባላቸው ምሁራን የተዘጋጀ እንደመሆኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት ቢሮዎች የተጋበዙት ከምሁራን ውይይት የሚገኘውን ግብዓት ለፖሊሲ ማበልፀጊያና የተሻለ አፈፃፀም እንዲወስዱ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል:: የመድረኩ ተሳታፊዎች ስብጥር አብዛኛውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ በመሆኑ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ ወደፊት መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ለማመላከት እንደሚጠቅም ፕ/ር ዘለቀ ጨምረው ገልጸዋል።

የቀድሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚደንት እና ከጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች አንዱ የነበሩት ፕ/ር ንጋቱ ረጋሳ በዕለቱ ውይይት የሚካሄድባቸው አጀንዳዎች ወቅታዊና የመንግስትን ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ጠቁመው በሀገር አቀፍ ደረጃ የመውለድ ምጣኔው ቀደም ሲል ከነበረው ጊዜ የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም ከፍ ያለ ቁጥር ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል:: ፕ/ር ንጋቱ የህዝብ ቁጥር እድገትን በአዎንታዊ መልኩ መጠቀም እንደሚገባ፣ የሀገር ውስጥ የስራ ዕድልን በማስፋት ወጣቶች ስደትን እንደ ብቸኛ አማራጭ እንዳይመለከቱ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመድረኩ ከተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል አሁን ያለው ነባራዊ ተግዳሮት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ፍጆታና የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ አለመመጣጠን ሲሆን ተስፋው ደግሞ የስነ ህዝብ ሽግግር፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግርየ፣ ተመቻቸ የፖሊሲ ስነ ምህዳር (ጤና: ትምህርት: መልካም አስተዳደር ወዘተ)፣ ሴቶችን በማብቃት የተሻሉ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል፣ የሚድያ ተደራሽነት እና የትምህርት አቅርቦትን ማሻሻል፣ የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ ለማምጣት የባህል ለውጥና ማሻሻያ ማድረግ ይጠቀሳሉ::

በማጠቃለያው ህዝብ መብዛት በራሱ ችግር ባይሆንም ካለው ሀብት አንፃር ካልተመጣጠነ የችግር መንስኤ እንደሚሆን እና ሰዎች በስደት ውስጥ ሆነው እንኳን ሕጋዊ ጥበቃና ድጋፍ ከተደረገላቸው ውጤታማና ለሀገራችን ልማት በጎ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እንደሚችሉ ተጠቅሷል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et