Skip to Content

DZ Cross- 387 መስራች የጤፍ ዝርያ የደረሰበትን ደረጃ ለማየት በአርሶአደሮች ማሳ የመስክ ምልከታ ተደረገ::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአለታ ጩኮ ወረዳ ጉንዴ ቀበሌ በ16 አርሶ አደሮች በ10 ሄክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም የለማውን DZ cross-387 መስራች የጤፍ ዝርያ ማላመጃ የምርምር ሥራ የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት የተዘጋጀው የመስክ ምልከታ በዓል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ህዳር 3/2019 ዓ.ም ተካሂዷል።


የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ተወካይ ፕ/ር መብራቱ ሙላቱ በመስክ ምልከታው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ከለያቸው የትኩረት ዘርፎች መካከል አንዱ በሆነው የሰብል ልማት ዘርፍ መስራች ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በስፉት ተደራሽ ለማድረግና ለማላመድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በጉንዴ ቀበሌ የ16 አርሶ አደሮችን ማሳ በመጠቀም ላለፉት ወራት መስራች የጤፍ ዝርያውን በስፉት የማምረቱ የሙከራ ስራ ውጤታማ እንደሆነ መታዘባቸውንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በበኩላቸው cross- 387 መስራች የጤፍ ዘር ቀደም ሲል በአካባቢው አርሶ አደሮች ጥቅም ላይ ውሎ የማያውቅ በመሆኑ ለቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት አመታት መስራች ዘር ሆኖ በስፉት የማባዛት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው ወደ ምርት ገብቶ እስኪሰራጭ ድረስ ከልማት ሰራተኞች ጋር በጋራ በመሆን የሚደረገው ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


ቀደም ሲል በበቆሎ ዝርያ ላይ በጋራ የመስራት ልምድ ከዩኒቨርሲቲው ጋር መኖሩን በማስታወስ አርሶአደሩ አዳዲስ ዝርያዎችን የመቀበል ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአለታ ጩኮ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ዮሴፍ ጋርሳሞ ሲሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠል ምርታማነትን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።


የጉንዴ ቀበሌ ኗሪ የሆኑትና በኩታ ገጠም የመስራች ጤፍ ዝርያውን በድጋፍ አግኝተው እያለሙ ከሚገኙት አርሶአደሮች መካከል ወ/ሮ ከበቡሽ ፉጤ እና አቶ ተሾመ ቡሬ በጋራ በሰጡት አስተያየት ስለተደረገላቸው የምርጥ ዘር ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ከጤፍ ዝርያው የተሻለ ምርትን እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

Share this post
Tags
Archive
Canadian Foreign Affairs Leadership, Hawassa University College of Medicine & Health Sciences discuss Partnership for Healthcare Excellence