በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንስቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ከ "Operation Smile Ethiopia" በተባለው ግብረሰናይ ድርጅት በተመደበ 52 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ማዕከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እና የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በተገኙበት ሚያዝያ 23/2018 ዓ/ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመሯል።
በጤና ሚ/ር ሚንስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የህብረተሰቡን የጤና ችግሮች ለማቃላልና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋግጥ መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ግብረ-ሠናይ ድርጅቶችን በማስተባበር በሚደረገው የጋራ ጥረት ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ ለመሆኑ የዚህ ዘመናዊ ሕክምና ማዕከል መሰራት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። "ኦፕሬሽን ስማይል ኢትዮጵያ" ከአሁን ቀደም በጅማና መቀሌ ሲሰጥ የቆየውን የሕፃናት ክንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በቋሚነት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል መጀመሩ ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ለማሻሻል እያካሄደ ለሚገኘው የሪፎርም ስራዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ዶ/ር ደረጀ ገልፀዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ በተፈጥሮ ከጤና እክል ጋር የሚወለዱ ሕፃናትን የመደበቅ የቆየ ጎጅ ልማድ መኖሩን ጠቅሰው በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካይነት ቤት ለቤት በተሰጠ ትምህርታዊ ገለፃ እጅግ በርካታ ሕፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን መቻለቸውን ገልፀዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ሆስፒታሉ ደረጃውን የሚመጥን አገልግሎት ለኅብረተሰቡ እንዲሰጥ የዩኒቨርስቲው አመራር ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር: ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም የሆስፒታሉን እድሳት ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅና በቦታ እጥረት ምክንያት የተፈጠረውን የግቢ መጨናነቅ ለማስቀረት ተጨማሪ ግንታዎችን ለማካሄድ ጥረት የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በኦፕሬሽን ስማይል ለተደረገው ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ማሽነሪዎች ድጋፍና ተከላ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የሀዩ-ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍጹም ወ/ገብርኤል በሰጡት የማጠቃለያ ንግግር ሆስፒታሉ በሪፌራል ደረጃ ከ18 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን እንደሚያገለግል ገልፀው በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ውስብስብ የቀዶ ህክምና አገልግሎቶች እየሰጠ እንደሆነ ተናገረዋል:: ከኦፕሬሸን ስማይል ኢትዮጵያ የተገኘውና ከ52 ሚሊየን ብር በላይ በሚገመት ድጋፍ የተሰራው የቀዶ ሕክምና ማዕከል ለሆስፒታሉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ዶ/ር ፍፁም ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው 150 ሕፃናት ተለይተው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ከዶ/ር ፍጹም ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።
