በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ እና በሲዳማ ክልል የእንስሳት ልማት ቢሮ ትብብር የአለም የወተት ቀንን ምክንያት በማድረግ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአርቢዎችንና የባለድርሻ አካላትን ትስስር ለማጠናከር ታልሞ ለአራት ቀናት ለወተት አምራቾች ሲሰጥ የቆየው ስልጠናና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ሰኔ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠናቋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በማጠቃለያው መድረክ ላይ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 50 ዓመታት በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ በርካታ ችግር ፈቺ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው ዋነኛ የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አድርጎ በለየው የግብርና፣ የእንስሳት ሀብት እና ተዋጽኦ ምርት ላይ በምርምር የተደገፉ እሴቶችን በመጨመር ይበልጥ ተጠቃሚ የሚኮንበትን ስራ እየሰራ ይገኛል። ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም የወተት ምርት በቀጥታ ለሰው ልጆች ፍጆታ የሚውል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የምርት ሂደቱ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን በመገንዘብ የወተት አምራቾቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ቀድሞም ከነበራቸው ግንዛቤ ጋር በማስተሳሰር የትሻለ ውጤታማ ሥራ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የሲዳማ ክልል የእንስሳት ልማት ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር ሚሊዮን ዮቴ በበኩላቸው በ“ሌማት ትሩፋት” የሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የወተት ልማትን ማሳደግ መቻሉ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀዋሳ ከተማ ያለውን ከፍተኛ የወተት ፍጆታ እና ጥራት ፍላጎት ለማሟላት በዝርያ ማሻሻል ሥራ ላይ ይበልጥ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲዎችና በመንግሥት መዋቅር መካከል የነበረው መራራቅ ተቀርፎ በአሁኑ ወቅት ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በቀጣይም የወተት ምርታማነትን ብሎም በአጠቃላይ በእንስሳት ሀብት ዘርፍ ያለውን ምርት ለማሳደግ ቢሯቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ የእንስሳት ልማት ቢሮ ጋር በመሆን የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ የወተት አምራቾችም የተሰጣቸውን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር ምርትን በየደረጃው ማሳደግ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የምርምር ቡድኑ አስተባባሪና ዶ/ር ስንታየሁ ይግረም ናቸው።
ስልጠናው ቀደም ሲል በልምድ ብቻ ከሚሰሩበት አሰራር ወጥተው የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ ማስቻሉን የወተት ምርት አምራቾቹ የገለጹ ሲሆን በመድረኩ የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንደ ግብአት በመውሰድ፣ በቀጣይ በጥናትና ምርምር የተደገፉ የተግባርና የክህሎት ስልጠናዎች ለአምራቾች መሰጠታቸው እንደሚቀጥል ተነግሯል።
