Skip to Content

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ለ45 ቀናት ያሰለጠናቸውን 120 የከተማ መሬት ፕላንና ፋይናንስ ባለሙያዎች አስመረቀ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የከተማ መሬት ፕላን እና የከተማ ፋይናንስ ዘርፎች ላይ ከሲዳማ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የከተማና መሬት አስተዳደር ቢሮዎች ለተውጣጡ 120 ባለሙያዎች ለ45 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ግንቦት 26/2018 ዓ/ም ተጠናቋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ፋንታ ደጀን በምረቃው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ፣ ማራኪ እና አስፈላጊ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል በእውቀት እና በሙያ መመራት አለባቸው ብለዋል:: ሚኒስትር ደኤታው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ቢኖራቸውም እንኳን የሠዎችን እንቅስቃሴ በአግባቡ በመምራት ተምሳሌት የሆኑትን የጃፓን ከተሞች ተሞክሮ አንስተው ከተሞቻችን ምቹ እንዲሆኑ የምናደርግበት ምክንያት ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ ሲመጡ የተሻለ ኑሮ ደረጃ እንዲኖራቸው ጠብቀው እንደመሆኑ ያንን ማሟላት የመንግስት ግዴታ መሆኑን ገልፀዋል:: ያንን ለማድረግ ደግሞ ከተሞች ራሳቸውን እንዲችሉ ገቢ ማመንጨት የግድ ስለሆነ የገቢውን አስተዳደር በእውቀት መምራት እንዲቻል ይሄ በአምስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ የተሰጠው ተግባር ተኮር ስልጠና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ፋንታ ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት 10 ቢሊየን የነበረው የኢትዮጵያ ከተሞች ገቢ ዘንድሮ ወደ 80 ቢሊየን ማደጉን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ደኤታው ቀደም ሲል ስለ ከተሞች ልማት የነበረው አረዳድና ግንዛቤ በቂ እንዳልነበረ ጠቅሰው አሁን ላይ ግን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጀምሮ እንደሃገር የከተሞች ዕድገትና ዘመናዊነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራ በመሆኑ ግዜው ለሰልጣኞቹ ሙያቸውን በቀጥታ ወደ መሬት ለማውረድ ብሎም ከሌሎች ባልደረባዎቻቸው ጋር እውቀታቸውን እንዲያጋሩ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ይሄንን እንዲተገብሩ አደራ ብለዋል።

የወ/ደ/ተ/ሃ/ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወልደአማኑኤል በበኩላቸው ኮሌጁ በመደበኛው የመማር ማስተማር እና የምርምር ስራዎቹ ካለው ዘመን ተሻጋሪ አበርክቶ ባሻገር ከተሞችን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ፕላን ኖሯቸው ውብ አረንግዋዴና ለመኖሪያ ምቹ ማድረግ በሚቻልበት ብሎም የከተሞችን ገቢ በዕውቀት ለማስተዳደር የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን በየዓመቱ በማሰልጠን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ትብብር እንደሚያጠናክር ገልፀዋል:: ኮሌጁ ተግባር ተኮርና ዘመኑን የዋጀ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ ስልጠና በመስጠት ባለሙያዎች ራሳቸውን እንዲያሻሽሉና ሙያዊ አበርክቷቸውን ለሀገራቸው ልማት እንዲያውሉም አደራ ብለዋል።

የስልጠናውን ይዘትና አካሄድ በተመለከተ የኮሌጁ መሬት አስተዳደርና ቅየሳ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አባይ አስረስ ገለፃ አድርገዋል።

በማጠቃለያው ፕሮግራም ላይ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂምን ጨምሮ የሶስቱም ክልሎች የከተማና መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Share this post
Tags
Archive
Wondo Genet College of Forestry and Natural Resources Hosts the 3rd Annual Research Conference