Skip to Content

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸዉን 3,317 ተማሪዎች አስመረቀ።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ27ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 3,317 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ እና በሦስተኛ ዲግሪ ያስመረቀ ሲሆን በተጨማሪም በምህንድስና ትምህርት፣ ምርምር እና ዓለምአቀፍ ትብብር ዘርፎች ለዩኒቨርሲቲው ያደረጉትን የላቀ አስተዋፅኦ ምክንያት በማድረግ ለጀርመናዊው ፕሮፌሰር ዶ/ር ኢ/ር ዮሐንስ ሽታይንብሩን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል::


በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የከብር እንግዳ የሆኑት የሐዋሳ ከተማ አሰተዳድር ከንቲባ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ፣ የፌደራልና የሲዳማ ክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲዉ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች፣ ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።


ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሐዋሳ ክተማ ዕድገትና በጎ ለውጦች ጋር ያላችዉን ጥብቅ ትስስር በማስታወስ ዩኒቨርሲቲዉ ለሀዋሳ ከተማ ሁለንተናዊ እድገት በምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ለግማሽ ምዕተ አመት የቆየ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ከንቲባው አክለውም ተመራቂዎች በቀጣይ በሚሰማሩብት የሰራ መስክ ሀገራቸዉን በትጋትና በመልካም ሥነ ምግባር ሊያገለግሉ እንደሚገባ አስገንዝበዉ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸዉ ያገኙትን ዕዉቀት ለሌሎችም እንዲያካፍሉና ለዩኒቨርሲቲዉም ሆነ ለሀዋሳ ከተማ የአምባሳደርነት ሚናቸዉን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው 3 ሺህ 317 ተማሪዎች መካከል 26 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀው ወቅቱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምስረታውን 50ኛ አመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር እየተዘጋጀ እና ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር ጫፍ ላይ የደረሰበት እንደሆነ ተናግረዋል:: የዩኒቨርሲቲው ስኬትና ጥንካሬ በሚያስመርቀው የተማሪ ቁጥር ብዛት ብቻ የሚለካ እንዳልሆነ የገለፁት ዶ/ር ፍስሃ የተቋሙ እውነተኛ ስኬት የሚመዘነው ጥራት ባለዉ ትምህርት አሰጣጥ፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን፣ በፈጠራ ስራዎችና በማህበረሰቡ ላይ በሚፈጥረዉ በጎ ተጽዕኖ መሆኑን አስገንዝበዋል።


የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የነበሩት እና ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኃላም ጭምር ለተቋሙ የምህንድስና ትምህርት ዘርፎችን በማስፋፋት፣ በምርምርና ፈጠራ፣ እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለምአቀፍ ትብብሮችን በማምጣት ለዩኒቨርሲቲው እድገት ያደረጉትን የላቀ አስተዋፅኦ ምክንያት በማድረግ ለጀርመናዊው ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጂነር ዮሐንስ ሽታይንብሩን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል::


በዕለቱ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል፣ 2, 666 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 289 በሁለተኛ ዲግሪ፣ 73 በፒ.ኤች.ዲ፣ 79 በህክምና ስፔሻሊቲና፣ 1 በህክምና ሰብ ስፔሻሊቲ እንዲሁም 211 በልዩ ልዩ የመምህርነት ሙያ ስልጠና ዘርፎች የሰለጠኑ ተመራቂዎቸ ሲሆኑ ከየኮሌጁ እና ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ማዕረግ ላስመዘገቡ ተማሪዎችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Share this post
Tags
Archive
A high-level delegation led by Hawassa University President Visits Norway