Skip to Content

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 251 ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ከኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) ህፃናት መንደር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በጨፌ ኮቲ ጀዌሳ ቀበሌ ነዋሪ ሆነው ከ8 የተለያዩ ት/ቤቶች ለተወጣጡ 251 የትምህርት ግብአት እጥረት ያለባቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችና የሴቶች ንጽህና መጠበቅያ ድጋፍ አድርጓል።


የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ትምህርት ለየትኛውም ሀገር እድገት ዋና መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው ከኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) ህፃናት መንደር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ ትምህርትንና ተማሪዎችን በቋሚነት ሲደግፍ መቆየቱን ገልጸዋል። በተለይም በ2019 የትምህርት ዘመን ይህን ድጋፍ በልዩ ሁኔታ በማጠናከር ለተማሪዎቹ የመማሪያ ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስ፣ ቦርሳ እና ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማበርከቱንና በተጨማሪም 12ኛ ክፍል ተፈትነው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ላላስመዘገቡ የአካባቢው ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ታፈሰ አረጋግጠዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው በትምህርት ሚኒስቴር ስር ባሉ 47 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና 3 ተጠሪ ተቋማት (በአጠቃላይ 50 ተቋማት) እያንዳንዳቸው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 100 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እንዲያቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግን ይህ አቅጣጫ ከወረደበት ጊዜ አስቀድሞ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ድጋፉን ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።


ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት መምሪያው በሚተገበሩ ፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆን በዘርፈ-ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶች አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል ያሉት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ብርሃኑ ደሳለኝ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን እውቀትና ልምድ ወደ ታችኛው የትምህርት እርከን ማሸጋገር ይቻል ዘንድ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


የኤስ.ኦ.ኤስ ህፃናት መንደር ፕሮግራም የሀዋሳ ማስተባበሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ግርማ ሞገስ ደግሞ በጋራ በሚተገበረዉ ፕሮግራም የመማሪያ ቁሳቁስ በማቅረብና ስልጠና በመስጠት ዩኒቨርሲቲዉ ድጋፉን እንደሚያሳይ በእነርሱ በኩል እንደዚሁ ከልጆች አስተዳደግና ከትምህርት ጋር በተያያዘ፣ የቤተሰብና የማህበረሰብንም አቅም ከመገንባት አኳያ በርካታ ስራዎችን እየተሰራ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።


ይህ የትብብር ፕሮጀክት ለረጅም ዓመታት ለአካባቢው ማህበረሰብ የትምህርት መርጃ መሳሪያና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ከማበርከቱ በተጨማሪ በጨፌና ቆንቦኦ የተለያዩ ደረጃዎች ያሉትን የመማሪያ ህንፃ በመገንባት ለማህበረሰቡ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የጨፌ ኮቲ- ጀቤሳ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ዘለቀ ማርሳሞ ናቸው።

Share this post
Tags
Archive
15ኛው ዙር ብሔራዊ የሰላም በጎ ፈቃድ አገልግሎት የስልጠና ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሄደ።