Skip to Content

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ኮምፕሪሄንስቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዓመታዊ የህሙማን ደህንነት ቀን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል "ደኅንነቱ የተጠበቀ እንክብካቤ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች" በሚል መሪ ቃል ዓመታዊ የህሙማን ደህንነት ቀን የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።


የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍጹም ወ/ገብርኤል በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የበዓሉ ዋነኛ ዓላማ በህክምና ሂደት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ መጉላላቶችና ስህተቶችን በማረም ሕግና መመሪያን በተከተለ መልኩ ህሙማን ፈጣንና ተገቢውን አገልግሎት እንድያገኙ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር በሽታን ጨምሮ የኩላሊት፣ የልብ፣ የስኳርና ደም ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፍጹም ከጉዳዩ አሳሳቢነት በመነሳት መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ዩኒቨርስቲው በዘርፉ የሚካሄዱ ምርምሮችን ለማስፋት ቅድሚያ መስጠቱን ጠቁመዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በመድረኩ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት የሀገሪቱን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ወሳኝ በመሆኑ የጤናው ዘርፍ መንግስት በትኩረት ከሚያከናውናቸው አስቻይ ጉዳዬች የቅድሚያ ቅድሚያ የተሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።


ዩንቨርስቲው በኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ አማካይነት ለሲዳማ ክልልና አጎራባች የኦሮሚያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሪፈራል ደረጃ መጠነ ሰፊ አገልግሎቶችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ም/ፕሬዝዳንቱ ዲጅታላይዜሽን፣ የፎረንሲክ አገልግሎት፣ የኩላሊት እጥበት፣ የኦክስጅን ማምረቻና የካንሰር ህክምና ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል።


የሲደማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ በማጠቃለያ ንግግራቸው የኅብረተሰቡን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቅድመ ጤና ምርመራ ግንዛቤ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመው የሪፈራል ጫናውን ለመቀነስ ክልሉ የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎችና አጠቃላይ ሆስፒታሎችን አቅም በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።


በፕሮግራሙ ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ በሰብ-ስፔሻሊስት ሀኪሞች የተዘጋጀ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የካንሰር ህክምና ማዕከል አገልግሎት ጉብኝትና ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋጾኦ ላበረከቱ አካለት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

Share this post
Tags
Archive
የቴማቲክ ምርምር ፕሮፖዛሎች የማጠቃለያ ግምገማ ተካሄደ።