የሰላም ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያካሄደው 15ኛው ዙር ብሔራዊ የሰላም በጎ ፈቃድ አገልግሎት የስልጠና ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሲዳማ ክልል እና የሀዋሳ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ በድምቀት ተካሂዷል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመክፈቻ ንግግራቸው የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት የሰው ልጅ ከሰው ተለይቶ መኖር የማይችልና የጠነከረ የህይወት መስተጋብር ያለው ማህበራዊ ፍጥረት መሆኑን በስፋት እንደሚናገሩ በመጠቆም ይህንን መስተጋብር በአግባቡ ለመምራት በሰላም የመኖር ክህሎትን መላበስ እና መለማመድ የግድ እንደሚል ገልጸዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም የሰው ልጅ በግለሰብ ደረጃ ከሚኖረው ሰላም ባሻገር እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ሰላምን ለማስፈን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የአብሮነት እሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም የ15ኛው ዙር የሰላም በጎ ፈቃድ ሰልጣኞችም ይህንኑ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ ኮሚሽነር አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው ሰላም ድንበርን የሚሻገርና ሰፊ ተጽዕኖ ያለው ሁለንተናዊ መፍትሔ መሆኑን በመጠቆም፣ በጸጥታ አካላት ከሚሰራው ሰላምን የማስፈንና ሁከትን የመቆጣጠር ስራ ባልተናነሰ ወጣቶች ለሰላም ግንባታና ለህዝቦች አብሮነት የሚጫወቱት ሚና የማይተካ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የተማረ እና ብቁ ዜጋ ከማፍራት ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን ድርሻ የመወጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተረድተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያሳሰቡት የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት በኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ ክቡር አቶ ፍሬሰንበት ወ/ትንሳኤ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ በተካሄዱ መሰል ስልጠናዎች ወቅት ላሳየው የላቀ ትብብርና አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
"በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው 15ኛው ዙር የሰላም በጎ ፈቃድ አገልግሎት የስልጠና መርሃ-ግብር ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን በሰላም ግንባታ፣ በበጎ ፈቃደኝነት እና በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ በማሰልጠን ለሀገር ሰላምና አብሮነት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማስቻል ዓላማ ያለው ነው።
