Skip to Content

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የመምህራን ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የመምህራን ጠቅላላ ጉባዔ በዩኒቨርሲቲው ሥር በሚገኙ 7ቱም ግቢዎች የሚያስተምሩ መምህራን በተገኙበት መስከረም 6/2019 ዓ.ም በዋና ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በድምቀት ተካሂዷል።

በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ፣ ዩኒቨርሲቲዉ በ2018 በጀት ዓመት በአካዳሚክ፣ በምርምርና ትብብር እንዲሁም በአስተዳደርና ልማት ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራትና የተመዘገቡት ዉጤቶች የሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ፣ ባለ ድርሻና አጋር አካለት ተሳትፎ ዕዉን የሆነ በመሆኑ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።


ፕሬዝዳንቱ  ዩኒቨርሲቲው በ2019 ዓ.ም በየዘርፉ ለማሳካት ያቀዳቸውን ዐበይት ግቦችና አቅጣጫዎች በማብራራት መምህራኑ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ተጠያቅነትን ማረጋገጥ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥል ተናግረዉ፣ መምህራን ለሙያቸዉ፣ ተማሪዎቻቸዉን ለዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ በአጠቃላይ ታማኝ በመሆን አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል::

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ፍስሀ ጌታቸው በ2018 ዓ.ም የአካዳሚክ ካሌንደሩን በታቀደለት ጊዜ አስጀምሮ ለማጠናቀቅ የተደረገውን ጥረት እና ስኬት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ብክነትን ለመቀነስ የተሰራውን ስራ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ለመስጠት የመምህራንና ተማሪዎች አቅም መገንባት ላይ፣ አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት፣ በሀገር አቀፍ መዉጫ ፈተና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ላይ የታዩ መሻሻሎችን፣ በት/ት ዘመኑ  73 የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን እንዲሁም 9 መምህራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ማግኘታቸዉን አንስተዋል:: በ2019 ዓ.ም  የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን ቁጥር ለመጨመር፣ ለመምህራን አስፈላጊ የት/ት ግብዓቶችን በየደረጃዉ ለማቅረብና የተማሪዎችን ዉጤታማነትን ይበልጥ ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል::


የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ገለጻ፣  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዉጤት መመዝገቡን ጠቅሰዉ፣ የምርምር በጀት በፊት ከነበረዉ ትርጉም ባለዉ መልኩ እንዲጨምር መደረጉን፣ በምርምር ስራ ላይ የሚሳተፉ መምህራን ቁጥር ከፍ ማለቱን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ በመንግስት እና በትብብር የሚተገበሩ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ፕሮጀክቶች መከናወናቸዉን፣ 1ሺ የሚሆኑ የምርምሮ ጽሁፎች በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሄቶች መታተማቸዉን፣ የዩኒቨርሲቲዉንና የሀገሪቱን በጎ ገጽታ መገንባትና ለዓለም አቀፍ ትብብር በር የከፈቱ ግዙፍ ዓለምአቀፍ ጉባዔዎች መካሄዳቸዉን፣ ሀገራዊና ወቅታዊ  አጀንዳዎችን የዳሰሱ የፓናል ዉይይቶችና ፖሊሲ ገለጻዎች መካሄዳቸዉን እንዲሁም 3 አዳዲስ የምርምር ማዕከላት መመስረታቸዉን አንስተዉ፣ በ2019 በጀት ዓመትም መሰል ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል::


የዩኒቨርሲቲዉን የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ስራ እንቅስቃሴን በተመለከተ የዘርፉ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፣ የዘርፉን አሠራር በሕግና በሥርዓት እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመምራት የተከናወኑ ተግባራትን አንስተዉ፣ የሰዉ ሃብት መረጃ፣ ፋይናንስ፣ ግዥና ንብረት  አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዲጂታል መደረጉን፣ ሰፋፊ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ካምፓሶች መከናወናቸዉን ጠቅሰዋል:: በተያዘዉ በጀት ዓመት መማር-ማስተማሩን፣ ምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎችን የሚያግዙ ግብዓቶችን የማሟላት፣ በሂደት ላይ ያሉ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ፣ ከግዥ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን  ለመቅረፍ፣  በጀት አጠቃቀምን በእጅጉ ከፍ ለማድረግ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እና የተማሪዎች አገልግሎትን ለማሻሻል  ሰፋፊ ዕቅዶች መያዛቸዉን ተናግግዋል::


ከገለጻዎቹ በማስከተል በነበረዉ የዉይይት ክፍለ-ጊዜ መምህራን ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን፣ ከም/ፕሬዚደንቶቹ አስፈላጊው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው  የማጠቃለያ ሀሳብና የሥራ መመሪያ ስጥተዉ መድረኩ ተጠናቋል::

Share this post
Tags
Archive
Wondo Genet College of Forestry and Natural Resources Co-Organizes International Dialogue on Wildfire Management