Skip to Content

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ሽግግር ሂደት ላይ የውጭ ባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ራስገዝ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ለሚገኙ የውጪ ባለድርሻ አካላት በዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ሽግግር ዝግጅት ላየይ የግንዛቤ ማስጨበጫና ግብረመልስ ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል::

የዩኒቨርሲቲዉ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንትና ዶ/ር ኢንጅነር ፍስሃ ጌታቸዉ መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለፁት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 50 ዓመታት ዉስጥ ወሳኝ የሚባሉ ሂደቶችን አልፎ አሁን ደግሞ ሌላ የሽግግር ምዕራፍ ላይ የደረሰዉ ከበርካታ ዓለምአቀፍና ክልላዊ ባለ ድርሻና አጋር አካላት ጋር በፈጠረዉ ጠንካራ ተቋማዊ ትስስርና ትብብር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዉ በቀጣይ ወደ ራስ-ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲነት ለመሸጋገር እያደረገ ባለዉ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ከባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር መወያየት ያስፈለገውም ዓላማውን በግልፅ አስረድቶ አብሮ ለመስራት ወደ ጋራ ግብ ለመድረስ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል:: የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዕድገት ከየት ወዴት እንደሆነ ሲገልፁም የዛሬ 50 ዓመት ሥራ ሲጀምር ከነበረው 4 የዲፕሎማ ፕሮግራሞች ወደ 300 በላይ የትምህርት ፕሮግራሞች፣ ከ30 መምህራን ወደ 2000 በላይ መምህራን፣ ከ230 ተማሪዎች ዛሬ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ እና ዩኒቨርሲቲ ከሆነበት ግዜ ጀምሮ እንኳን እስካሁን ከ120 ሺህ በላይ ምሩቃንን ያፈራ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስረድተዋል::


የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ምንነት፣ የመንግስት ፖሊሲ አቅጣጫ፣ አስፈላጊነትና በሂደቱ ላይ የባለድርሻ አካላትን ሚና በተመለከተ የዩኒቨርሲቲዉ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንትና የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሽግግር ስትራቴጂ ቀረጻ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ አቅረበዋል፡፡ ዶ/ር ታፈሰ ባቀረቡት ጽሑፍ ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር ልማት ያላቸዉን ሁለንተናዊ እና አይተኬ ሚና ከተጨባጭ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች አንጻር አጉልተዉ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በተጨማሪም የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በሂደት ወደ ራስ-ገዝ ተቋምነት እዲሸጋገሩ መንግስት ፖሊሲ ቀርፆ አቅጣጫ ማስቀመጡንና በዚህም መሰረት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 50 ዓመታት በሰዉ ሃይል ልማት፣ በምርምርና ማህረሰብ አገልግሎት ለአካባቢዉ፣ ለሀገሪቱና ለዓለም ህዝቦች እያበረከተ የቆየዉን አስታዋጽኦ በማስረጃ አስደግፈዉ ያቀረቡት ዶ/ር ታፈሰ፣ በቀጣይም የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ቅልጥፍና፣ ዉጤታማነትና ጥራት ላይ መሥራት የሽግግሩ ዋንኛ ዓላማዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ራስ-ገዝ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃን መሸሻ በበኩላቸዉ የሽግግር ሂደቱ አራት ዓመታትን የፈጀ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ያካተተና በቀጣይ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የሙከራ ትግበራ ጊዜን የሚያልፍና ከዚያም ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ አካሄድ መሆኑን ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ አቶ ብርሃን አክለዉም ዩኒቨርሲቲዉ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ የሚጠበቅበትን እጅግ ዉስብስብና አድካሚ የሆኑ ወሳኝ ሂደቶችን ማጠናቀቁንና አሁን በ 2019 ዓ/ም ወደ ሙከራ ትግበራ ለመግባት የዩኒቨርሲቲዉ ሥራ አመራር ቦርድ አስተያየትና የትምህርት ሚንስቴር ዉሳኔን በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


ገለጻዎቹን ተከትሎ በተደረገዉ የተሳታፊዎች ዉይይት በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዉ ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷባቸዋል፡፡ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ወክለው የተገኙት የፕሬዝዳንቱ የኢኮኖሚ አማካሪ ክቡር አቶ ግዛቸው ኖኦራን ጨምሮ ከ64 የተለያዩ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ ተቋማት የተወከሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ዩኒቨርሲቲዉ እያደረገ ባለዉ ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ ላይ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉን አድንቀዉ በቀጣይ ቢሰሩ ያሏቸዉን ተግባራት ጠቁመዋል፡፡


ለአብነትም፡- ከተቀሩ ባለድርሻ አካላት ጋር መሰል ዉይይቶችን ማካሄድና ግንዛቤን መፍጠር፣ በአቅራቢያ ካሉ የተለያዩ ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር ስትራቴጅያዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርቦ በዘላቂነትና በትብብር መስራት፣ ዩኒቨርሲቲዉ የሚያስተላልፋቸዉን ዉሳኔዎችና የሽግግር ሂደቱን በተመለከተ ወቂታዊና በቂ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በመስጠት አሉባልታዎችንና የመረጃ ክፍተቶችን መቅረፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቁሟል:: በተለይ ደግሞ በማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚታዩ የዩኒቨርሲቲውን እውነታ የማይገልፁ አሉታዊ መረጃዎችን ለማጥራት መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በስፋት እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል::


በመድረኩ ማጠቃለያም የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተነሱትን አስተያየቶችና ጥያቄዎች በመቀበል በቀጣይ በየደረጃዉ በሂደት ለመስራት ጥረት እደሚደረግ ለመድረኩ ተሳታፊዎች አረጋግጠዉላቸዋል፡፡ በዚህም በተለይ "የበንሳ ዳዬ እና አዋዳ ካምፓሶች ሊዘጉ ነው" የሚል መሰረተቢስ ሐሰተኛ መረጃ በሰፊው እየተሰራጨ መሆኑ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ በግለሰቦች የሚደረግ ከንቱ ዘመቻ መሆኑን እና የራስገዝነት ሁለት ዋነኛ ኢላማዎች ጥራትን ማረጋገጥ እና ትብብርን ማጠናከር ብሎም እውቀትና ዓለምአቀፋዊነትን የተላበሱና መልካም ስነ ምግባር ያላቸው ምሁራንን ማፍራት ላይ መሆኑን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል::

Share this post
Tags
Archive
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ልማት ማህበር ጋር የእንሰት ሰብል ጥበቃ፣ ምርምር እና ስልጠና ማዕከል ምስረታ የትብብር ስምምነት ውል ተፈራረመ፡፡