በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከሲዳማ ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር “የኢትዮዽያ ሀገር በቀል እውቀት ስርአቶችን ለሰላም፣ ለአስተዳደር፣ ለፍተህ እና ለዘላቂ ልማት እንደገና ማዕከላዊ ማድረግ” በሚል መሪ ቃል የሲዳማ ክልል እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በመድረኩ ቁልፍ ንግግራቸው እንዳመለከቱት ሀገር በቀል እውቀቶች በመንግስት አስተዳደር፣ በጤና አጠባበቅ፣ በግብርና፣ በግጭት አፈታት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሴቶች ሚና ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ እሴቶች ያሏቸው እንደመሆኑ እነዚህን እውቀቶች በሳይንሳዊ መንገድ አጥንቶ በመሰነድ ተጠቃሚ መሆን ይገባል ብለዋል። ዶ/ር ታፈሰ አያይዘውም ሀገራችን ብዝሀ ብሔሮችን ያቀፈች በመሆኑ እያንዳንዱ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲጠቀምበት የነበረውን እሴት እርስበርስ በመለዋወጥ ለጋራ እድገት የማዋሉ ድርሻ የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕ/ር ዘለቀ አርፍጮ በበኩላቸው በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ለትውልድ የሚተርፉ በርካታ ጠቃሚና ሊዳብሩ የሚገባቸው ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳሏቸው ገልጸው በውይይት መድረኩ ላይ በሳይንሳዊ መንገድ የተጠኑ የሲዳማ፣ የኦሮሞ፣ የወላይታ እና የጌዴኦ ማህበረሰብ ሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት መካሄዱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለው የሲዳማ ጥናት ተቋም ተ/ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ አርጎ ስለ ሃገር በቀል እውቀት አስፈላጊነት በዩኒቨርሲቲው ታምኖበት ከዓመታት በፊት ተቋም ተመስርቶ የሲዳማን ባህል፣ ቋንቋ፣ የቀን አቆጣጠር፣ ስነ ህንፃ፣ ባህላዊ የመድኃኒት እፅዋት፣ የሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት እሴቶችን ለማጥናት እና ሰንዶ ለትውልድ ለማሻገር እየሰራ መሆኑን ገልፀው “የሴቶች ሚና በሀገር በቀል ሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት፤ የሲዳማ ያኮና የአርሲ ኦሮሞ ሀዳ ሲንቄ ሥርዓት ንጽጽራዊ ጥናት” በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል:: ዶ/ር አበራ ተቋማቸው በክልሉ የሚገኙ ሀገር በቀል እውቀቶችን በተደራጀ መልኩ የማሰባሰብ፣ የማደራጀትና የማስተዋወቅ ስራዎችን በትኩረት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቀው ከእነዚህም መካከል ባህላዊ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ሙዚየምና ቤተ-መጽሐፍት የመክፈት እንዲሁም የሲዳማ ቋንቋ መዝገበ ቃላት የማዘጋጀትና ሌሎች ተያያዥ ምርምሮችን በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
“በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ የሀገር በቀል እውቀትን እንደገና ማዕከላዊ ማድረግ፤ ከገዳ ስርአት ለስነ-ምግባር፣ ለዴሞክራሲ፣ ለግጭት አፈታት እና ለማህበራዊ አስተዳደር የሚገኙ ግንዛቤዎች” በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕ/ር አለሙ ኃይሉ ሲሆኑ የገዳ ስርአት ለዘመናዊው አስተዳደር ያለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አብራርተው በተጨማሪም የገዳ ስርአትን ተሞክሮዎችና ፍልስፍናዎች በኦሮምያ ክልል ወደ መደበኛው የትምህርት ስርአት ማስገባት የተቻለበትን መልካም ልምድና ሂደቶች በስፋት አጋርተዋል።
በዕለቱ ከቀረቡት የምርምር ጽሁፎች መካከል የዶ/ር መሸሻ መካ “የወላይታ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት እውቀትና ከዘመናዊው የፍትህ ስርአት ጋር ያለው ትስስር” እንዲሁም የአቶ ደሳለኝ በቀለ “የጌዴኦ ሀገር በቀል የመሬት ጥበቃና እንክብካቤ ስርአት” የሚሉት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በቀረቡት ጥናቶች ላይ ከተሳታፊዎች ሰፊ ውይይትና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
