ት/ሚኒስቴር የሀዩ የሪፎርም ጉዞ ላይ ውይይት አካሄደ

ትምህርት ሚኒስቴር የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ጉዞ ላይ ውይይት አካሄደ።

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር የተቋሙን የለውጥ ጉዞ በተመለከተ የግማሽ ቀን ውይይት በዋናው ግቢ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ባሉበት ወቅት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሃገርአቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እንዲተገበር የተዘጋጀውን የለውጥ እቅድ ተቀብሎ ለማስፈጸም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሐኑ ነጋ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የታሰበው ሪፎርም አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በውይይት ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ትም/ሚኒስቴር በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ተቋማቱን የመደገፍ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ በመስራት ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ እንዳለ የጠቀሱት ሚኒስትሩ "ዩኒቨርሲቲዎች በእውነትና በእውቀት ላይ ተመስርተው ሀገርን የመጠበቅ ልዩ ኃላፊነት ስላለባቸው ዓለም እየመጣባት ካለው የለውጥ ወጀብ ሀገራችንን ለመታደግ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት በመፍጠር መመከት እንድንችል የፊት መሪ መሆን ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትርና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የትምህርት ዘርፍ በሃገር ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ከሚገኙ የለውጥ ስራዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው የከፍ/ትም/ተቋማት እንደ ሀገር ማምጣት ለምንፈልገው ለውጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደር ናሲሴ "ችግሮችን ለመቅረፍ 'እንዴት እዚህ ደረስን?' ከሚለው ጥያቄ በላይ 'ወዴት እየሄድን ነው?' በሚለው ላይ አትኩረን ዩኒቨርሲቲዎቻችን አካዳሚክ የልህቀት ማዕከላት እንዲሆኑና ትውልድን በብቃት እንዲቀርፁ ብዝሃነትን የሚያስተናግድና ለለውጥ ዝግጁ የሆነ አመራር፣ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያለው እና ሰላማዊ የመማር ማስተማርና የምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ ማስቻል እንፈልጋለን" ብለዋል:: ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከእነዚህ መስፈርቶች አንፃር በጥንካሬ የሚነገርለት ጎን እንዳለው ሁሉ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል::

'ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ለመሆን በመሰረታዊነት የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት እና ብቁ የአስተዳደር መዋቅር ያስፈልጋቸዋል' ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኮራ ጡሹኔ የታቀደውን ሪፎርም ለመተግበር ያለፈውን አሰራር ለመኮነን ሳይሆን የተሻለ ጥራት ያለው አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ስለሆነ ከሁሉም የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ እንጂ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተለየ ችግር ስላለበት አይደለም ብለዋል::

በትም/ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲዎች አደረጃጀትና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ እንዳሉት መሰል ውይይት በሌሎችም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቀጥል እንደሆነና አላማውም ዩኒቨርሲቲዎች ካሉባቸው ውስስብስብ ተግዳሮቶች የሚወጡበትን መንገድ በማመላከትና የተሻለ ብቃት እንዲኖራቸው ለማስቻል አሁን ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር ያላቸውን ቁመና በጋራ ተወያይተን መስመር ማስያዝና ብቃታቸውን ለማረጋገጥ እንሰራለን ብለዋል::

በውይይት መድረኩ ከተሳታፊዎች በርካታ ሃሳቦች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et