ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ የመግባቢያ ሰነዱ በሚፈረምበት ወቅት እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍና በክልሎች ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የሚመጡለትን ጥያቄዎች በመቀበል፣ ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንፃር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀምና ኃላፊነት በመዉሰድ ለሀገር፣ ለተቋማቱ እና ለማህበረሰብ የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ምርምሮችንና የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በተጠየቀዉ ጥራትና ጊዜ በማድረስ የሚያስመሰግን ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አዉስተዋል:: ዶ/ር አያኖ ከዚህ ቀደም በቀድሞዉ የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል ጠያቂነት የተለያዩ መተግበሪያ ሶፍትዌሮችን በማልማትና በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ገብተዉ እየተሞከሩ ያሉ እንዲሁም በማለቅ ላይ ያሉ ሶፍትዌሮች እንዳሉም ገልፀዋል።
የደቡብ ክልል እንደ አዲስ በአራት ክልሎች ሲደራጅ ቀድሞ የተተገበሩትንና በማለቅ ላይ ያሉትን ሶፍትዌሮች እንደየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ሰርቶ ለማስረከብ ዩኒቨርሲቲው ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ቢሮዎችም እነዚህን ሶፍትዌሮች በልፅገዉና ለምተዉ በክልሉ አገልግሎት ላይ እንዲዉሉ ጥያቄ በማቅረባቸው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመተግበር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያሳዩትን ተነሳሽነት በማድነቅ በስምምነቱ መሰረትም ሶፍትዌሮቹ በዩኒቨርሲቲዉ ባለሙያዎች ተሰርተዉ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የገቢዎች፣ የዉሃ፣ መስኖ ማዕድን ልማት፣ የመንገድና ትራንስፖርት ልማት እና የንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከዚህ በፊት በተሰሩትና እየተሰሩ ባሉት ሶፍትዌሮች ላይ በዩኒቨርሲቲዉ የሶፍትዌር ባለሙያዎች ቡድን ገለፃ ተደርጎላቸዋል:: ከገለፃው በኃላ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ በክልሉ በኩል የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እነዚህ ሶፍትዌሮችን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ፣ ሙስናን ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላት ዝግጁ መሆናቸዉን በመግለፅ ኃላፊዎቹ የመግባቢያ ሰነዱን ከዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚደንት ጋር ተፈራርመዋል።