አውደ -ርዕይ ተካሄደ

በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ቀጠናዊ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል አውደ-ርዕይ ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር "ቀጠናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል በዓይነቱ ለየት ያለና በአካባቢው የሚገኙ የግልና የመንግስት ኢንዱስትሪዎችን ያሳተፈ አውደ ርዕይ አካሂዷል።

የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከ110ሺ በላይ ምሩቃንን በማፍራት የተማረ የሰው ኃይል በማብቃት: በርካታ ምርምሮችን በመስራትና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ለአካባቢው ብሎም ለሀገራችን እድገት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ እዚህ ደርሷል:: በአሁኑ ወቅትም በአቅራቢያው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋራ በመስራት አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመው እንደ ምሳሌ ከይርጋዓለም የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያና ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፖርኮች እንዲሁም ሌሎች የግል አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በአዋጅ በተደገፈ የሕግ ማዕቀፍ በተደረጉ ስምምነቶች መሠረት የተፈጥሮ አካባቢን ለጉዳት የሚዳርጉ ቆሻሻ ንጥረ ነገሮችን መልሶ በማልማት ለተሻለ አገልግሎት በማዋል እና በኮምፒዩተር መረጃ ደህንነት ዙሪያ መጠነ ሰፊ ስራዎች በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ታፈሰ አብራርተዋል።

ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግብርና: በጤና: በኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ: በማህበራዊ ሳይንስ: ህግና ስነሰብ እንዲሁም በትምህርት ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ወደ ሥራ ሲገባ ከሚጠበቅበት በርካታ ነገሮች መካከል ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በአጋርነት ተቀራርቦ መስራት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል::

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢ/ር ፋስካ ቤተ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኢንዱስትሪዎች በአካባቢያቸው ከሚገኙ የከ/ት/ተቋማት ጋር በትብብር እንዲሠሩ በመንግስት ህግ ከወጣ 35 ዓመታት ቢቆጠሩም ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም መመሪያ ባለመኖሩ ምክንያት በጋራ ጥቅሞች ላይ ያለመተማመን ተፈጥሮ መቆየቱን አስረድተው ይሄንን የሚቀርፍ አዋጅ ቁጥር 1298/2015 ከወጣ ወዲህ ግን በአከባቢው የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ገልፀዋል። ዶ/ር ፋሲካ የዕለቱን መርሃግብር አስመልክቶም ይሄ መነሻ እንጂ የመጨረሻው ባለመሆኑ በቀጣይ እጅግ ተቀራርበን የምንሰራው በጣም ብዙ ሥራ አለ ብለዋል::

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተሩ ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ለዘላቂ ልማትና ሀገራዊ ዕድገት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ እንደሀገር የተቀመጠውን የህግ ማዕቀፍ ይዘት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ም/ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ ግርማ ኢንስቲትዩቱ ከአጋር ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር ሊሰራባቸው የሚችልባቸውን ዘርፎችና ያለውን እምቅ አቅም ለተሳታፊዎች አብራርተዋል::

በዚህ አውደ ርዕይ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲና ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተጋበዙ የጨርቃ ጨርቅ ዲዛይንና ስፌት ተማሪዎች የፋሽን ትርኢት የቀረበ ሲሆን በሁለቱም ተቋማት ተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች እንዲሁም የቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ ያሉ የምርምርና ፈጠራ ሥራ መሰረተ ልማቶች ተጎብኝተዋል::

በፕሮግራሙ ላይ ከ150 በላይ የሚሆኑ ከሲዳማ ብ/ክ/መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፋ የስራ ኃላፊዎች: ከሀዋሳና ይርጋዓለም ኢንዱስትሪ ፖርኮች እንዲሁም ሌሎች ከግልና የመንግስት ኢንዱስትሪዎች የተወጣጡ ኃላፊዎችና የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ወደፊት በምን መልኩ አብረው መስራት እንደሚገባና ባሉ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል::

ዶ/ር ታፈሰ በውይይቱ ማጠቃለያ ንግግራቸው "ከዚህ በኃላ በከፍተኛ ጥራት የተማረና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ኢንዱስትሪው የሚፈልገው አይነት የሰው ኃይል በማፍራት: ችግር የሚተነትን ሳይሆን ችግር ፈቺ ምርምር በመስራት እንዲሁም ቴክኖሎጂና ፈጠራን በሚያበረታቱ አሰራሮች የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በመደገፍ ላይ ትኩረት ይደረጋል:: ለዚህም ዩኒቨርሲቲ እንደ እውቀት ምንጭ: ኢንዱስትሪው እንደ ካፒታል ባለቤት እና የፖለቲካ አመራሩ ደግሞ ለሕዝብ የገባው ኃላፊነት እንዳለበት ባለድርሻ አካል የሶስቱ ቅንጅትና ተናብቦ መስራት አሁን ግዜው የሚጠይቀው አካሄድ ነው" ብለዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et