ፊቼ ጫምባላላ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሲምፖዚየም ተከበረ::

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሲዳማ ዘመን መለወጫ 'ፊቼ ጫምባላላ' መጋቢት 26/2016 ዓም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በደማቅ ሲምፖዚየም ተከብሯል::

የበዓሉን ሲምፖዚየም ያዘጋጀው የሲዳማ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ስዩም ዩንኩራ ተሳታፊዎችን እንኳን አደረሳችሁ ካሉ በኃላ የሲዳማ ሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ሰጥተው በዓሉን አስጀምረዋል::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ተወካይና የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ ሲምፖዚየሙን ሲከፍቱ እንዳሉት ፊቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ ለሰው ልጅ ባለው ክብር ማለትም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ማንም ሰው ቂምና ጥላቻን አስወግዶ በይቅርታ እንዲሻገር የሚያስገድድና ሰላምን የሚያውጅ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የብሔረሰቡ አባላት በሻፌታ ዙርያ ተሰብስበው ሲመገቡ የሚፈጠረው የአንድነት: የፍቅር: የመተባበር እና የመጋራት እሴቶች ናቸው:: ዶ/ር ታፈሰ በንግግራቸው ከዘመናዊ ትምህርት ርቀው እየኖሩ በተፈጥሮ ባገኙት ጥበብ ሰማይና ጨረቃን አንብበው ይሄንን ልዩ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖር ዘመን ተሻጋሪ አሻራ ያኖሩ የሲዳማ አባቶችን በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት አመስግነዋል::

ፊቼ ጫምባላላ የሚከበርበት የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የጨረቃ ዑደትን የሚከተል ውስብስብ የስነ ፈለክ ዘዴ መሆኑን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪው ዶ/ር አመሎ ሶጌ ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጋር የሰሩትን ጥናትና ምርምር ውጤት ለበዓሉ ታዳሚዎች አቅርበዋል:: በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ የቀን አቆጣጠር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁት የጎርጎርሳውያን እና የሂጅራ ዘመን አቆጣጠር በምን መልኩ ከሲዳማ ብሔር የቀን አቆጣጠር ጋር እንደሚመሳሰሉና እንደሚለያዩ ሰፊ ጥናታዊ ማብራሪያና ትንታኔ ሰጥተዋል::

በማስከተልም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ረ/ፕሮፌሰር የሆኑት ማቲዎስ ወ/ጊዮርጊስ በዓሉ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም እንዴት በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ እንደበቃ አብራርተዋል:: ከምክንያቶቹም መካከል የባህላዊ እሴቶች መኖር አንዱ መሆኑን ጠቁመው የበዓሉ ባህላዊ አከባበር ይዘት እና ክንውኖች ከተምሳሌታዊ ትርጓሜዎቻቸው ጋር ምን እንደሚመስሉ ዝርዝር ገልፃ ካደረጉ በኃላ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ውይይት ተደርጓል::

የሲዳማ ብሔር የሀገር ሽማግሌዎች: የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከሰባቱም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች የተውጣጡ በርካታ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የበዓሉ ታዳሚ ሲሆኑ 'ወሊማ የሲዳማ ባህላዊ ባንድ' ፕሮግራሙን በባህላዊ ሙዚቃና ጭውውት አድምቆታል:: በመጨረሻም የበዓሉ ታዳሚዎች ባህላዊውን ሻፌታ ተቋድሰው የበዓሉ ማሳረጊያ ሆኗል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et