የe-SHE ፕሮጀክት እና የመልቲ ሚዲያ ስቱዲዮ ምረቃ

የe-SHE ፕሮጀክት የክላስተር ዩኒቨርሲቲዎች የውይይት መድረክና የመልቲ ሚዲያ ስቱዲዮ ምረቃ ተከናወነ::

በትምህርት ሚኒስቴር መሪነት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን የፋይናንስ ድጋፍ፣ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ (ASU) ቴክኒካል ድጋፍ እና በሀገርበቀሉ ሻያሾኔ ኃ.የተ. የግ.ማህበር (SYS) ትብብር ለአምስት ዓመታት በ50 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተሰራበት ያለው በኢንተርኔት የታገዘ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ያተኮረው e-Learnig for Strengthening Higher Education (e-SHE) ፕሮጀክት የክላስተር ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ውይይት መድረክ የክላስተሩ መሪ በሆነው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመጋቢት 20/2016 ዓም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በዕለቱም በዚሁ ፕሮጀክት የተገነባው መልቲሚድያ ስቱድዮ ተመርቋል::

የሀዩ አካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍስሀ ጌታቸው በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት e-learning የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅና ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው በመታወቁ ይህንን አሰራር በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ገልጸው ይህንኑ ስራ የe-SHE ፕሮጀክት በበላይነት እያስተባበረ እንደሚገኝም አብራርተዋል። ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም የዛሬው መድረክ የእስካሁኑ የዩኒቨርሲቲዎች የe-SHE ፕሮጀክት የሶስት ወራት አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግምገማ የሚደረግበትና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ስር ከሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እየተሰራ ያለውን ስራ ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግበት ተናግረዋል።

የe-SHE ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ባስሊዮስ ጥላሁን በበኩላቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በሁሉም ደረጃ በሚገኙ የሀገሪቱ የትምህርት ሴክተሮች ላይ የመማር ማስተማር ሂደትን የማስቀጠል ችግር በመፈጠሩ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመን ተደራሽና የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚቋቋም የትምህርት ሂደት ለመዘርጋት በማሰብ ፕሮጀክቱ መጀመሩን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በዚህ ቆይታው ውስጥ 50 በላይ ዩኒቨርስቲዎችን፣ ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎችን፣ ከ35 ሺህ በላይ መምህራንን እና አምስት የመልቲ ሚዲያ ማዕከላትን ለማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ አስተባባሪው ጨምረው ተናግረዋል።

የሀዩ e-learning ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የe-SHE ፕሮጀክት ማዕከል እንዲሆኑ ከተመረጡ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ስራ ለማሳለጥ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ስራውን የሚመራ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ዳይሬክተሩ ጨምረው ለሁለት ቀናት በሚቆየው መርሀግብር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ስር የሚገኙ አስሩ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንዲጠቀሙበት የተገነባው የመልቲሚዲያ ስቱዲዮ እንደሚመረቅና የጋራ የአጠቃቀም መመሪያው ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የዚህ ፕሮጀክት ቁልፍ አላማ ከሆኑት ውስጥ የከ/ት/ተቋማትን በዘመኑ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ የመጠቀምና የአገልግሎት ተደራሽነትን በማጠናከር ጥራትን ማሻሻል እንዲሁም የሰው ሀብት አቅም ግንባታ መሆኑን የጠቆሙት የሻያሾኔ ኃ/የ/የግል ኩባንያ ኃላፊ አቶ ያሬድ ሰርፀ በተለይም በመምህራን የዲጂታል የትምህርት ይዘት ዝግጅትና አሰጣጥ: የተማሪዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት አጠቃቀም እንዲሁም የአይ ሲቲ ሲስተም አስተዳዳሪዎች የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራ ገልፀዋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኃላፊዎች፣ የe-SHE ፕሮጀክት መልቲሚድያ ስቱድዮ ማዕከላት የሆኑት የአምስቱም ዩኒቨርሲቲዎች የአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክተሮች እና አስተባባሪዎች እንዲሁም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ስር የሚገኙት የአርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወራቤ፣ ዋቸሞ፣ ጅንካ፣ መደወላቡ፣ ቦረና፣ ቡሌ ሆራ፣ እና ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲዎች የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተሮች፣ የአይ ሲ ቲ ዳይሬክተሮች እና የኢለርኒንግ አስተባባሪዎች በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮጀክቱ የተገነባውን ስቱድዮ በጋራ የሚጠቀሙበት እንደመሆኑ የአጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ንድፈ ሃሳብ በፕሮጀክቱ አማካሪ ዶ/ር ለማ ለሳ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል::

በመጀመሪያው ቀን ውሎ ማጠናቀቅያ ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በተገኙበት የሀዩ መልቲሚድያ ስቱድዮ ምረቃ ተከናውኗል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et