ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጦርነት ለተጎዱ ሶስት ዪኒቨርሲቲዎች ድጋፍ አደረገ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጦርነት ለተጎዱ ሶስት ዪኒቨርሲቲዎች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ፡፡

በኢትዮጵያ አሸባሪው ህወሃት ኃይል በተለያዩ ክልሎች ላይ ወረራ በማካሄድ በርካታ ጥፋቶችን እና ውድመቶችን ማስከተሉን ተከትሎ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዚያቶች ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የብርና የደም ልገሳ ድጋፍ እንዲሁም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአፋርና ደብረብርሃን ከተማ በአካል በመገኘት የአልባሳት፣ የምግብ ግብዓትና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ከጥር 27/2014ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደግሞ በአማራ ክልል ወሎ ዞን ውድመት ለደረሰባቸው መቅደላ አምባ፣ ወሎ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችና ኮምፒውተሮችን አበረከተ፡፡

ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እና የዩኒቨርሲቲው ተወካይ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት በጦርነቱ ከወደሙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል  እንድናደራጅ በትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት የተሰጠን መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲን ቢሆንም የእኛ ዩኒቨርሲቲ ግን በራሱ ተነሳሽነት ሌሎቹን ሁለት ዩኒቨርሲቲዎችንም በቻለው መጠን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል፡፡ አክለው እንደተናገሩትም ግምታቸው 11ሚሊ. 984ሺህ ብር የሚሆን የኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂና ፊዚክስ ቤተሙከራ መሳሪያዎች፣ የምግብ ቤት ዕቃዎችና ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች ለመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ለእያንዳንዳቸው ግምታቸው 1.4 ሚሊ. ብር የሚሆን የቤተሙከራ መሳሪያዎች ለወሎ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች አበርክተናል ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰኢድ እንደገለፁት የት/ት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ድጋፍና መልሶ ማቋቋም እንዲያደርጉልን የተመደቡ ዩኒቨርሲቲዎች ቢኖሩም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ለየት የሚያደርገው ከተመደበለት ዩኒቨርሲቲ ውጪ በርካታ የላብራቶሪ ዕቃዎችን ድጋፍ ስላደረግልን እና ለሌሎችም ተምሳሌት በመሆኑ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ታምሬ ዘውዴ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ወራሪው ኃይል የተለያዩ ህንፃዎችን፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ በርና መስኮቶች፣ የላብራቶሪና የቢሮ ዕቃዎችን እና ኮምፒውተሮችን በማውደምና በመዝረፍ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ ማድረሱን ገልፀው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም በርካታ የላብራቶሪ ዕቃዎችና ኮምፒውተሮችን ድጋፍ በማድረጉ አመስግነው ዩኒቨርሲቲያችን የኢትዮጵያ ልጆች የሚማሩበት በመሆኑ የዚህ መሰሉ ትብብርና ድጋፍ አንድነታችንን ያጠነክረዋል ብለዋል፡፡

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አበበ ግርማ በበኩላቸው በተደረገላቸው የሳይንስ ላብራቶሪ ዕቃዎች ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀው እንደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም  መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ሶስቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከየካቲት ወር ጀምሮ በየደረጃው ተማሪዎቻቸውንን ተቀብለው ማስተማር እንደሚጀምሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et