ሀዋሳ ዩኒቨርሲት ከሲዳማ ክልል አደጋ ስጋት የስራ አመራርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በፊርማ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎችን በጥናትና ምርምር ተደግፎ የአደጋውን ስፋት ከመቀነስ አልፎም ከተከሰተ ፈጣንና ስልታዊ ምላሽ የሚሰጥበት ዘዴ ላይ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በሲዳማ ክልልም የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ በጥናትና ምርምር፣ ግንዛቤ በማስጨበጥና በተክኖሎጂ የተደገፈ ምላሽ ለመስጠት ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ነው ነው ያሉት።

የሲዳማ ክልል አደጋ ስጋት የስራ አመራርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሃይሉ ሃሰና በበኩላቸው ኮሚሽኑ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የሚከሰቱ የአደጋ ስጋቶች ቅድመ ጥንቃቄ ለማከናወን ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመስራት፣ ለዓቅም ግንባታና ሀብት ለማፈላለግ ከዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የተገባ ስምምነት ነው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ደግሞ ስምምነቱ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይና እንዳስፈላጊነቱ የሚታደስ መሆኑን ጠቁመው በሁለቱ ተቋማት ትብብር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የክልሉን የአደጋ ስጋት ለመቀነስ ይሰራል ብለዋል።
