በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት በዩኒስኮ የተመዘገበው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል ዋዜማ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ መጋቢት 4/2018 ዓ.ም የብሔሩን እሴቶች ባንጸባረቀ መልኩ በድምቀት ተከበሯል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ጥናት ኢንስቲትዩት ተዘጋጅቶ በዓሉ በዩኒስኮ የማይዳሰስ የባህል ቅርስ መዝገብ ላይ እንዴት እንደተካተተ ጥናታዊ ፅሁፍ ገለጻ የተደረገበትና በሁሉም ኮሌጆች የተዘጋጀው የፍቅርና የአንድነት መገለጫ የሆነው የሲዳማ ባህላዊ ምግብ "ሻፌታ" በጋራ የቀረበበት የ2018 M.D የፊቼ ጫምባላላ ሲምፖዚየም በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ተጀምሮ በባህላዊ ሙዚቃ: ድራማና ቄጣላ ዝግጅቶች ታጅቦ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ስዩም ዩንኩራ የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በUNESCO ከተመዘገበ አስራ አንድ አመቱን ማስቆጠሩን አስታውሰው በእነዚህ አመታት ውስጥ ይህንን ዓላማ ለማሳካት በተቋሙ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መቆየታቸውንና በዚህም መሰረት ከበዓሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰነዶችንና የባህል ዕቃዎችን አሰባስቦ የያዘ ቤተመጻሕፍትና ሙዚየም ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል ። ዶ/ር ስዩም አክለውም ተቋሙ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ከት/ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሀገር በቀል እውቀት ዶክመንቴሽን ላይጥናት ለማድረግ በሲዳማ ክልል በተመረጡ 10 ወረዳዎች፣ በ4 ከተማ አስተዳደሮችና በሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ የጥናት ርዕሱ ላይ ያተኮሩ መጠይቆችን ወደ ሲዳማ አፎ በመተርጎም በዘመን አቆጣጠር፣ በስነ ከዋክብት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጤና አጠባበቅ፣ በሰላም ግንባታ፣ በግጭት አፈታትና ፍትህ ላይ ለባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቶ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

የሀ/ዩ/ አካ/ጉ/ም/ ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሐ ጌታቸው በበኩላቸው ሁሉም ህዝቦች የየራሳቸው የሆነ ባህልና እሴት እንደሚኖራቸው ይህንንም አስደማሚ ባህል በጋራ በማክበር የባህል ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ አስታውሰው ይህ እንዲህ በደመቀ ሁኔታ የምናከብረው በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታላቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል። ም/ ፕሬዝደንቱ አክለውም “ፊቼ” የሚለው ስያሜ በሀገሩ ባህል መሠረት አንድ ሴት ልጅ ትዳር መስርታ ከወጣች በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ ቡርሳሜ በወተት አዘጋጅታ ዘመዶቹዋን፣ ጎሮቤት ወዳጆቿን የምትጋብዝበት፣ ሰላምን፣አንድነትና ይቅርታን የያዘ ድንቅ በዓል በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው መከበሩ ተቋሙን ሁሉንም ባህሎች ያቀፈ የኢትዮዽያዊነት ማሳያ ያደርገዋል ብለዋል።
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በዩኒስኮ በማይዳሰስ የባህል ቅርስነት መመዝገብ ያለውን ጠቀሜታ አስመልክቶ በዶ/ር አበራ አርጎ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቶ ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች ላይም ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ የዕለቱ ፕሮግራም ሻፈታ በመጋራት ተጠናቋል።
Ayidde Chambalaalla!
Fichee Jeeji!
