በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰብ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ያስመረቃቸውን ጨምሮ በሕክምና ስፔሻሊቲ፣ በሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ እና በሌሎች የጤና ሳይንስ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 249 ወንዶች እና 178 ሴቶች፣ በአጠቃላይ 427 የጤና ባለሙያዎችን ዛሬ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና መሠረት መሆኑን ጠቁመው በተለይም መንግሥት በጤናው ዘርፍ ለሚሰጠው ልዩ ትኩረት ተመራቂዎች የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ኮምፕርሔንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሲዳማና የአጎራባች ክልሎች ኩራት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሰላማዊት፣ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ የሚያስመርቃቸው ባለሙያዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጤናውን ዘርፍ በብቃት እያገለገሉና እየመሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመክፈቻ ንግግራቸው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ስኬታማ ከሆኑ የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በያዝነው አመት ለሚያከብረው የ50ኛ አመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በአልና የራስ ገዝነት ሽግግር በልዩ ሁኔታ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ኮሌጁ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር በሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን የህክምና አገልግሎቶች በቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ለማዘመን የማስፋፍያ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የኮሌጁ ቺፍ ኤግዘክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍፁም ወ/ገብርኤል በበኩላቸው የሕክምና ትምህርት በአለም አቀፍ ደረጃ ፈታኝና ከፍተኛ ትጋትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው ተመራቂዎቹም ትምህርቱ የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍለው ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው ኩራት ለመሆን ለዚች ቀን ስለደረሱ በራሳቸው ሊኮሩ እንደሚገባና ያስተማረቻቸውን ሃገር ዜጎች በሙያቸው የላቀ አገልግሎት ለመስጠት እንዲዘጋጁ አደራ ብለዋል። ዶ/ር ፍጽም ኮሌጁ በኮምፕሪሔንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታሉ አማካይነት በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የህብረተሰብ ክፍል የካንሰር ጨረር ሕክምና፣ የፎረንሲክ ምርመራ፣ የስነ-ምረዛ እና የጨቅላ ሕጻናት ሕክምናን ጨምሮ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛውን ውጤት (CGPA 3.76) በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶ/ር ኤፍሬም ብዙአየሁ እንዲሁም ከጤና ሳይንስ ፕሮግራሞች CGPA 3.96 በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ኦስማን መዲድ፣ እና ከሴቶች በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛውን ውጤት CGPA 3.55 በማስመዝገብ የተመረቀችው ዶ/ር ሔርሜላ ገዛኸኝ፣ ከአጠቃላይ የትምህርት ፕሮግራሞች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሴት ተማሪዎችን ጨምሮ ከዕለቱ የክብር እንግዶች እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
ተመራቂዎች በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!
