በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለአዳዲስና ነባር ሰራተኞች በመሠረታዊ የንድፈ ሀሳብና የክህሎት ማሻሻያ ላይ ያዘጋጀው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ልምድ ባካበቱ የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሐ ጌታቸው ስልጠናውን ሲያስጀምሩ እንዳሉት በቅርቡ በተካሄደው የሰራተኞች ምደባ መሰረት ከተለያዩ ክፍሎች አዳዲስ አባላት የቤተመጽሐፍት አገልግሎቱን የተቀላቀሉ እንደመሆኑ 'የሚሰሩበት ከባቢ ምን ይመስላል?' ከሚለው ጀምሮ እንዴት ደንበኞቻቸውን ሊያገለግሉ እንደሚገባ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የቤተመጽሐፍት አገልግሎት በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዝዳንቱ ተጠቃሚዎቹም ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች እስከ አንጋፋ ተመራማሪዎች የሚደርስ በመሆኑ ሁሉንም ተጠቃሚ በበቂ ሁኔታ ማርካት የሚችል የዘመነ አገልግሎት ተግባራዊ ወደማድረጉ መገባቱን አክለዋል።
የቤተመጽሐፍት አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ተውልኝ ከበደ በበኩላቸው ስልጠናው በአራት ዙሮች ተከፋፍሎ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው በመጀመሪያው ዙር ለአዳዲስ የቤተመጽሐፍት ሰራተኞች፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ለነባርና አንጋፋ ሰራተኞች ፣ ሶስተኛውና አራተኛው ደግሞ በቂ የስራ ልምድ ላላቸው ባለሙያዎች እንደሚሰጠና የጠቅላላ ሰልጣኞች ቁጥር 210 እንደሚደርስ ገልጸዋል። ዘመኑ የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ በሁሉም ዘርፎች ላይ ጎልቶ የሚታይበት እንደመሆኑ የቤተመጽሐፍት አገልግሎት አሰጣጣችንን ለማዛመንና የተቀላጠፈ ለማድረግ ስልጠናው ተጨባጭ ሚና እንደሚጫወት ዶ/ር ተውልኝ ጨምረዋል።
በግብርና ኮሌጅ የቤተመጽሐፍት እና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ኃላፊና ተጋባዥ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ አሴር ሚልክያስ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን ይህንን የሚደግፉ አጋዥ መጽሐፍት ብሎም የምርምር ማጣቀሻ ሊሆኑ የሚችሉ ግብአቶችን ከሟሟላት ባሻገር አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች የቤተመጽሐፍት መሰረታዊያን እንዲሁም የዘመኑን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መላመድ የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።