የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ አመራርና ሰራተኞች ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።
ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ አመራርና ሰራተኞች "Public entrepreneurship and innovative ecosystem building" በሚል መሪ ቃል በዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕሩነርሽፕ ማበልፀጊያ ማዕከል የተዘጋጀና ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና እየወሰዱ ነው::
የኢንተርፕሩነርሽፕ ማበልፀጊያ ማዕከል አስተባባሪና አሰልጣኝ ወ/ሮ ትዕግስት አሰፋ እንደተናገሩት የአሁኑ ስልጠና በዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ ሶስተኛው ዙር መሆኑን ጠቅሰው ቀደም ብሎ ለመካከለኛ አመራሮች በሁለት ተከታታይ ዙሮች ተሰጥቷል። በአሁኑ ዙር 50 የሚደርሱ የኢንተርፕራይዙ ሰራተኞች ስልጠናውን እየወሰዱ እንደሆነና የስልጠናው ግብ ተቋሙ አሰራሩን በመፈተሽ ክፍተቶችን ለይቶ እንዲያወጣ በማስቻል እሴት የታከለበት የፈጠራ አሰራር ዘርግቶ የሚያስገባውን ገቢ እንዲያድግ ማስቻል መሆኑን ወ/ሮ ትዕግስት አክለዋል።
የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድሙ አክሊሉ በበኩላቸው የተቋሙ መመስረት ዋነኛ አላማ ዩኒቨርሲቲው ያለውን በርካታ የገቢ ማስገኛ የውስጥ አቅሞች በአንድነት ወደ አንድ መስመር በማሰባሰብ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል። የንግድ ስርዓት በባህሪው ብዙ ውድድር የሚበዛበትና ልቆ መገኘትን የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ወንድሙ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመገኘት የኢንተርፕራይዙን ስራዎች ማዘመንና ከገበያው ጋር ተስማሚ ለማድረግ ይሄ ስልጠና አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል።