የተማሪዎች አገልግሎት ሰራተኞች አመታዊ ጉባኤ ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ የ2016 ዓ.ም አጠቃላይ አፈጻጸምን በመገምገም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ የነበሩትን በማሻሻል የአዲሱን አመት እቅድ በተሻለ ብቃት ለመፈጸም በሰራተኞች መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ጉባኤ ዛሬ በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል።

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ተገልጋዮች የሆኑትን የተማሪዎችን የምግብ፣ የመኝታና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያሳልጡት ሰራተኞች ዋነኛ የዩኒቨርሲቲው ሀብት መሆናቸውን ገልጸው ባለፉት አመታት ላከናወኗቸው ስራዎች ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል። ዶ/ር ሳሙኤል ጨምረውም የተማሪዎች አገልግሎት ስራ በባህሪው ያለመቆራረጥ በየዕለቱ የሚከወን በመሆኑ ብዙ ተግዳሮቶች የሚገጥሙበት ቢሆንም ተገቢውን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት በማሳየት የአዲሱን አመት ዝግጅት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ዶ/ር አመሎ ሶጌ በበኩላቸው ጉባኤው ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በመገምገም የሰራተኞችን ግብረ መልስ ለመቀበልና ለአዲሱ አመት የተሻለ ለመዘጋጀት እንደሚረዳ ገልጸው በስራ ሽግሽግ ዘርፉን ለተቀላቀሉ አዳዲስ ሰራተኞች ደግሞ የስራ መመሪያ ገለጻ መደረጉን ተናግረዋል።

የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዲን አቶ አስማማው ደምሴ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ተቋማዊ ተግባሩን እንዲወጣ ከሚያስችሉ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ከ980 በላይ ሰራተኞችን የያዘው የተማሪዎች አገልግሎት አንደኛው መሆኑን አስታውቀው በየአመቱ አዳዲስ ተማሪዎችን ከመቀበላቸው በፊት ተመሳሳይ ውይይቶችን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

ለመደበኛ ተማሪዎች ከሚቀርበው አገልግሎት በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው የሚከወኑ ሀገር አቀፍ ሁነቶችን በስኬት ለማከናወን በሚደረገው ስራ ውስጥ የአገልግሎት ዘርፉ ትልቅ ድርሻ በመውሰድ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ተመራጭ እያስደረገ እንደሚገኝም አቶ አስማማው አክለዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et