ፕሬዝዳንቱ የአሰራር ስርዓትን በመከተል ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳሰቡ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታዉ አየለ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ተጠሪ የስራ ዘርፎችን ከሚመሩ የስራ አስፈፃሚዎች፣ ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች ጋር በሴኔት መሰብሰብያ አዳራሽ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሁሉም የሥራ ዘርፎች ላይ አግባብነት ያለው የአሰራር ሥርዓትን ተከትለው በተጠያቂነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል::
ዶ/ር ችሮታዉ ከተሳታፊዎች ጋር ትዉዉቅ ካደረጉ በኃላ የውይይት መድረኩ አስፈላጊነት በቅርበት ለመተዋወቅና በትኩረት መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የስራ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ መሆኑን ገልፀዉ ሁሉም ኃላፊዎችና በስራቸዉ ያሉ ሰራተኞችም የአሰራር ስርዓትን በመከተል፣ ዘርፉን በመደገፍ፣ በማቀድ፣ በመተግበር፣ የተሰሩትንም በመሰነድና ሪፖርት በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መመሪያ ሰጥተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አደቶ በበኩላቸዉ ፕሬዝዳንቱ ለስራ ዘርፎቹ ትኩረትና ጊዜ ሰጥተዉ በማናገራቸዉ አመስግነዉ በተለያዩ ክፍሎች የመዋቅር ለዉጥ እየተተገበረ በመሆኑ ያልተሟሉ መደቦች ቢኖሩም ባለዉ የሰዉ ኃይል ስራዎች ታቅደዉ መሰራና በየሶስት ወሩም ሪፖርት ተደርገዉ መገምገም እንዳለባቸዉ አስምረውበታል::
በዉይይቱም የየዘርፉ ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች አሰቸኳይና ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን አንስተዋል።