የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁላ ወረዳ የአርሶ አደሮች በዓል አከበረ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት በሁላ ወረዳ በአዶላ ኩራ እና በጋንጁሬ ጪጮ ቀበሌዎች እየሰራ ያለውን ትሪትካሌ የተሰኘ የስንዴ ሰብል ዝርያ የምርምር ውጤቶችን በተመለከተ የመስክ ጉብኝት በማድረግ የአርሶ አደሮች በዓል በ21/3/2010 ዓ.ም አከበረ።

ዶ/ር ተስፋዬ አበበ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት በበዓሉ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሰባት ዓመታት በዚሁ ወረዳ በርካታ የምርምርና ቴክኖሎጂን የማስተሳሰር ስራዎችን በስንዴ፣ በብቅል ገብስ፣ በምግብ ገብስ፣ በእንስሳት ሃብት፣ በተፈጥሮ ሃብት እና በመሳሰሉት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዕለቱም የተካሄደው የመስክ በዓል በአካባቢው ያለው የስንዴ ሰብል በዋግ በሽታ የሚጠቃና ምርታማነቱም ከአፈሩ አሲዳማነት / ኮምጣጣነት የተነሳ አመርቂ ስላልሆነ ይህንን የተሸለ ውጤት ያለውን የትሪትካሌ ስንዴ ዝርያ የማላመድና ውጤቱንም ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም የተገኙትን ተሞክሮዎች በማስፋት በዚሁ ወረዳ በተሳታፊ አርሶ አደሮች በኩል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ በሂደት ለመቀየር የሚያስችል በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ቴክኖሎጂዎቹን በማስቀጠሉ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የተመራማሪ ቡድኑ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ደመላሽ ከፋለ እንደገለጹት ትሪትካሌ ከስንዴ የምግብ ጥራትን ከሬይ ደግሞ የመቋቋም ባህሪያትን የያዘ ውህድ ዝርያ ሲሆን በእነዚህ ቀበሌዎችም አራት አይነት የትሪትካሌ ዝርያዎችን ማለትም ዘንካቴ፣ ሜኒት፣ ደረሰልኝና ሳናን የተባሉትን በምርምርና በተግባር በመስክ ላይ ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ዝርያዎች ናቸው ብለዋል።

ዶ/ር ደመላሽ አክለውም ፕሮጀክቱ አራት ዓላማዎችን አጣምሮ የያዘ ሲሆን ዝርያው አመራረቱ እንዴት ነው፣ ከምርቱ ምን አይነት ምግቦች ሊዘጋጁ ይችላሉ፣ ተረፈ ምርቱስ ለእንስሳት መኖ እንዴት ይውላል እና ህብረተሰቡስ በውጤቱ ምን ያክል ተጠቃሚ ይሆናል የሚለው በቡድኑ በቅደም ተከተል እየተጠና ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስክ ጉብኝቱም ከተካሄደ በኋላ አርሶ አደሮቹ ዝርያውን በተመለከተ እንደሌላው ጊዜ በወረዳው ተመርጦልን የመጣ ሳይሆን በተግባር ዩኒቨርሲቲው በማሳችን ላይ ሞክሮና ተመራምሮ በማሳየት ውጤቱም አመርቂና ምርታማ መሆኑን በዓይናችን እንድናየው በማድረጉ እናመሰግናለን ያሉ ሲሆን አርሶ አደር ግርጃ ጦና እና አሰፋ ቦኮ ምርቱን ለማስፋት ዘሩ እንዴት እንደሚገኝ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀሙን በተመለከተ እና ከተመረተስ በኋላ የገበያ ትስስሩ እንዴት እንደሚሆን ጠይቀው ዶ/ር ደመላሽ ሲመልሱ ምርምሩ ገና የተጀመረ እንጂ ያላለቀ በመሆኑ በሰፊው ከአርሶ አደሮቹ ጋር በመስራት የዘር ብዜትን፣ የማዳበሪያ አጠቃቀምን እና ከተመረተ በኋላም የገበያ ትስስሩን በተመለከተ ከክልሉ፣ ከዞኑና ወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ጋር ወደፊት በመስራት ምላሽ የሚገኝበት ይሆናል ብለዋል።

                                                                                                               በስለሺ ነጋሽ

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.