ከ74ሺ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደረገው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት የመስክ ጉብኝት ተደረገ

በደቡብ ክልል አንደንድ አከባቢዎች ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተነሳ በጨቅላ ሕፃናት ላይ ጎልቶ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ላለፉት 5 ዓመታት በተካሄደ ፕሮጀክት ከ74 ሺ በላይ አባ ወራ አርሶ አደሮችና ከፍል አርብቶ አደሮች የሰብል አመራረትና አመጋገብ ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉ መደረጉን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ላለፉት 30 ዓመታት በእርሻ ዘርፍ በከፍተኛ ተመራማሪነት እያገለገሉ የሚገኙና በአሁኑ ወቅት የካናዳ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሸለመ በየነ እንዳስታወቁት መቀንጨር ዋነኛ ችግር የነበረው በየዕለቱ ህጻናቱ ከሚመገቡአቸው ምግቦች የፕሮቲን፤ብረትና ዚንክ ንጥረ ነገሮች መጓደል መሆኑን በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ የአከባቢው አርሶ አደሮች ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን በጥምር እርሻነት እንዲያመርቱ ላለፉት 7 ዓመታት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን የተሻለ ውጤትም እንደተመዘገበ ገልፀዋል፡፡

በዚህም መሰረት በክልሉ ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው የሲዳማ፤ ጌድኦ፤ ወላይታ፤ ጉራጌና ስልጤ ዞኖች እንዲሁም አላባ ልዩ ወረዳ ከሚገኙ የግብርናና ጤና ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት በተደረገ እንቅስቃሴ ክፍተኛ የምግብ ይዘት ያላቸውን አዳዲስ የበቆሎ፤ ቦሎቄና ሽንብራ ዝርያዎችን በማከፋፈል በተሻለ መልኩ የሚመረቱባቸውን ሁኔታዎች ከማመቻቸት በተጨማሪ አዳዲስ የአመጋገብ ዘዴዎችን በማስተማር በተደረገ ጥረት የተሻለ ውጤት ለማግኘት መቻሉንና በአሁኑ ወቅት በአካባቢዎቹ የሕፃናት የዕድሜና ቁመት መመጣጠን እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ74 ሺ በላይ አባወራ እና እማወራ አርሶ አደሮች በፕሮጀክቱ አማካይነት ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ በአከባቢቸው ለሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮች ተሞክሮዎቻቸውን በማስፋት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ሸለመ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎችንም ለመድረስና የአፈር ለምነት ምርምር ስራዎችን ባካተተ መልኩ የአርሶ አደሩን የአመራረትና አመጋገብ ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ የሚረዱ አዳዲስ ተጨማሪ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውንና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተመከረባቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በካናዳ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ምርምር ፈንድ ድጋፍ እንዲሁም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የካናዳው ሳስካችዋን ዩኒቨርሲቲ ጥምረት ከዓለም አቀፍ የልማት ምርምር ማዕከል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት 7 ዓመታት ሲካሄድ በቆየው በዚህ የምርምር ፕሮጀክት እንዲሁም ላለፉት 20 ዓመታት ከሳስካችዋን ዩኒቨርሲቲ ጋር በተሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሮቹ ሕይወት ከመለወጡም ባሻገር 121 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በምርምር ስራው መሳተፋቸውንና ከነዚህም መካከል 12ቱ ለዶክትሬት ቀሪዎቹ ለሁለተኛ ዲግሪ የሚያበቃቸውን የመስክ ምርምር በማካሄድ አጥጋቢ ውጤት ማግኘታቸውን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ አበበ በመስክ ጉብኝቱ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ከተጠቃሚ አርሶ አደሮች መካከል በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጎጌት አንድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስናፍቅሽ ሻንቆ እና ኬላ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ክበበው ኤዳኦ በሰጡት አስተያየት እያመረቱ ያሉትን የሽንብራና የቦሎቄ ምርቶች ለገበያ አቅርበው ከፍተኛ ገቢ እያገኙባቸው ከመሆኑም በላይ በገንፎ፣ ቂጣ፣ ሾርባና ዳቦ መልክ እያዘጋጁ ለልጆቻቸው እየመገቡ መሆኑንና የልጆቻቸው ጤንነት መሻሻሉን አስረድተዋል፡፡

በዕለቱም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች፣ ከአጋር ድርጅቶችም፡ ICRISAT - International Crops Research Institute for the Semi-Arid Tropics, ICARDA - International Center for Agricultural Research in the Dry Areas, ከደቡብ ክልል ግብርናና ጤና ቢሮዎች፣ ከደቡብ ክልል የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ፌዴሬሽን እንዲሁም ከደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ተቋምና የተለያዩ የዞንና ወረዳ ቢሮዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

                                                                  በዳዊት በዳሳ  

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.