የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ9ኛ ጊዜ ተማሪዎቹን አስመረቀ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ9ኛ ጊዜ ጥር 06/2010 ዓ.ም 26 ሴቶችን ጨምሮ 138 ተማሪዎቹን በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ በኮሌጁ ኣዳራሽ በደማቅ መርሐ-ግብር አስመረቀ ። አቶ አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት በዕለቱ ተገኝተው የዕለቱን እንግዶች፣ ተመራቂዎችን፣ የተመራቂ ቤተሰቦችን እና መላውን የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ዩኒቨርሲቲው በአገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የመሆን ራዕይ አንግቦ እየሰራ መሆኑንና በመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል በተካሄደው የአጠቃላይ አፈጻጸም ድድር ለተከታታይ 5 ዓመታት ከ1-3 ያሉ ደረጃዎችን የወጣና ከፍተኛ እውቅና እያገኘ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚደንቱ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እየተከናወኑ ካሉ አንኳር አንኳር ተግባራትን ካነሱ በኋላ ጤናን በተመለከተም ለረዥም ጊዜያት ሲሰራበት የነበረው ሆስፒታል መሰረታዊ እድሳት ያስፈለገው በመሆኑ በዚሁ ላይ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን፣  በመፋጠን ላይ የሚገኘው የካንሰር ማዕከል ግንባታ በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ መድረሱንና በቅርቡም የቁሳቁስና የሰው ኃይል በማሟላት ስራ በማስጀመር ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ፣ ለኮሌጁና ሆስፒታሉ መስፋፋት በመሰረታዊ ችግርነት የሚታየውን የቦታ ጥበት ለመቅረፍም ከዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ጀርባ በተወሰደው መሬት ላይ የሚከናወን ግንባታ ዲዛይን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ልምዶችን ጭምር በመቀመር እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አቶ አያኖ በመጨረሻ እንደተናገሩትም አገራችን ካላት ውስን ሃብት ውስጥ በርካታውን ለትምህርት በመመደብ ተመራቂዎቹ የትምህርትን ዕድል በሰፊው እንዲያገኙ በማድረጓ እነርሱም ያገኙትን ዕውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ለሃገራቸው ህዳሴና ዕድገት በማበርከት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ በበኩላቸው ለተመራቂዎች እንደተናገሩት "ዛሬ እየተመረቃችሁ ያላችሁት መንግስት ለወጣቶች እንዲሁም ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት እየሰጠ ባለበት፣ ሃገራችን ኢትዮጵያም የዓለምን ትኩረት በእጅጉ እየሳበች እና ተደማጭነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ስለሆነ እድለኞች ናችሁ፡፡" ካሉ በኋላ አገራችን በተለያዩ ገጽታዎች በርካታ አንጸባራቂ ድሎችን እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸው  ከጤና ጋር የተያያዘውን ብቻ ለማንሳት ሃያላን ከሚባሉት ሃገሮች ሳይቀር ተወዳድረን የዓለም ጤና ድርጅትን እንድንመራ በከፍተኛ ድምጽ የተመረጥንበት ወቅት በመሆኑ በትጋትና በቅንነት ከሰራን "ይህስ አይታሰብም" የሚባል የትኛውም ከፍታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሌለ ያረጋገጠልን ታላቅ እውነታ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ተመራቂዎቹ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ለዚያ ቀን ያበቋቸውን ወላጆቻቸውንና አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ታላቅ አደራ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዶ/ር አቤል ገደፋው በምክትል ፕሬዚደንት ማዕረግ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር  በበኩላቸው እንደተናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምናው ዘርፍ የተጣለበትን ብቁ የህክምና ባለሙያዎች የማፍራት ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ ለመማር ማስተማር፣ ለምርምርና ጥናት እንዲሁም ለማህበረሰብ አገልግሎት ትኩረት በመስጠት በክልላችንም ሆነ በአገር ደረጃ ያለውን የህክምና ባለሙያ ዕጥረት ለመቅረፍና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በዕለቱ የተመረቁትን 138 የህክምና ዶክተሮች ሳይጨምር ከ2001-2009 ዓ.ም ራሳቸውን ጨምሮ በጠቅላላ 679 የህክምና ዶክተሮችን አስመርቆ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ደረጃዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ህብረተሰቡን እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ኮሌጁና ሆስፒታሉም አገልግሎታቸውን በማስፋትና በማጠናከር በቅርቡ የኩላሊት እጥበት ህክምናን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከሁለት ቀናት በፊት ጥር 04/2010 ዓ.ም ዓመታዊ የሰራተኞች በዓሉን ለ5 ጊዜ መላው ሰራተኞቹና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ማክበሩንና በተለያዩ ምድቦችም የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ያላቸውን ሰራተኞቹን መሸለሙ የታወቀ ሲሆን ይኸው መልካም ተግባር የሰራተኛውን የስራ ሞራል የሚያነሳሳ በመሆኑ በሌሎችም ሊሰፋ እንደሚገባ መገለጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በስለሺ ነጋሽ

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.