12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

‹‹በህገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል 12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአገር ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎችና መርሐ-ግብሮች መከበሩ የሚታወስ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ትምህርታዊ የፈጠራ ስራዎችን ባካተተ መልኩ በተመሳሳይ ድምቀት ተከበረ፡፡ በዚሁ መርሐ-ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት /ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ  እንደተናገሩት የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ብዝሃነትን በመቀበልና ራስን በራስ አገርን በጋራ በማስተዳደር ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ግብ ያደረገ በመሆኑ በሁሉም ዘርፍ ለውጥና ዕድገት ለማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓታችን ዜጐች የጋራ ጉዳያቸውን በሚመለከት በፌዴራላዊ ስርዓት የሚተዳደሩበት እና በየአካባቢያቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ነፃነት ያጐናፀፍቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው የመማር የመዳኘትና ባህላቸውን የማሳደግ መብት ያጎናፀፋቸው በመሆኑ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም ድህንነት እና ኋላቀርነትን በመቅረፍ ላይ በማተኮር ባለፉት ዓመታት ሲደረጉ የቆዩ አገራዊ ትግሎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የተናገሩት ኃላፊው በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ትንንሽ ግጭቶችን የብሔር መልክ በማላበስ የግጭቱን ምንጭ የፌደራል ሥርዓቱ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉም ዜጎች ሊያወግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዬች ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የፕሬዚዳንት ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር ኢንጂነር ፍስሐ ጌታቸው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የምሁራን መፍለቅያ እንደመሆናቸው መጠን ህብረ-ብሔራዊነትን ማዕከል ያደረገ ድኀነትንና ኋላቀርነትን ለመታገል የሚያስችሉ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በስፋት በማካሄድ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የሁሉ መሰረት የሆነውን ሰላምን በጋራ በመገንባትና በመጠበቅ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መሰረት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች የመጡ 41 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከመጀመሪያ እስከ 3 ዲግሪ በስሩ በሚገኙ 6 ካምፓሶች በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ እነዚሁ ተማሪዎች በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ  ችግር ፈቺ ቴክኖሎጅ እንዲያፈልቁና እንዲያሸጋግሩ በትጋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር እና መምህር አቶ አማሎ ሶጋ በህገ-መንግስት እና የፌዴራል ስርዓታችን ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ እና በተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በንቃት የተሳተፉበት የጥያቄና መልስ ውድድር የቀረበ ሲሆን ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢኒስትቲዩት የስነ-ህንጻ (Architecture) ተማሪዎችም በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው የአገራችንን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የመኖሪያ ቤት እና አካባቢ ሞዴል ሰርተው ለታዳሚያን በከፍተኛ ደረጃ ቀልብን የሳበ ዓውደ-ርዕይ አቅርበዋል፡፡ በወቅቱም የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ለወደፊትም የሁሉም ዘርፍ ባለሞያዎች አገራዊ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓላት ሲከበሩ በየመስካቸው በፌዴራላዊ ስርዓቱ የተገኙ ትሩፋቶችንም ሆነ ለወደፊት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ሳይንሳዊ ስራዎችን እየሰሩ ሁሉን አቀፍ ልማቱ ላይ አሻራቸውን ሊያሳርፉ እንደሚገባ ተገልጾአል፡፡

በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር፣ መምህራን የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች የተሳተፉ ስሆን ከሀዋሳ ኤስ ኤስ / ቤት ተጋብዘው የመጡ ሕፃናት በዕለቱ የተለያዩ ትርዒቶችን ማቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                                                                                              በዳዊት በዳሳ

 

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.