የካስኬፕ ፕሮጀክት አገልግሎቱን ከእጥፍ በላይ ማሳደጉን አስታወቀ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የካስኬፕ ፕሮጀክት ባለፈው ኀዳር 9-10/2010 ዓ.ም. በሲዳማ ዞን ጎርቼ እና በጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳዎች እያካሄዳቸው የሚገኙ የቢራ ገብስ፤ ስንዴ፣ ባቄላና በቆሎ አምራች አርሶ አደሮች የማሳ ጉብኝት አካሄደ፡፡

በወቅቱም የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅና ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ እንደገለጹት የካስኬፕ ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲው አስተባባሪነት በደቡብ ክልል አራት ዞኖችና አምስት ወረዳዎች ብቻ ሲካሄድ የቆየውን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ የማስፋት ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስድስት ዞኖችና አስራ ሶስት ወረዳዎች ተደራሽነቱን የማሳደግ ስራ ተከናውኗል፡፡

 

ፕሮጀክቱ በዋነኛነት በክልሉ እየተተገበረ ያለውን የግብርና ዕድገት ፕሮግራም በመደገፍ የሚሰራ ሲሆን በቅንጅት በሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሲዳማ፣ በጌዲኦ፣ በስልጤ፣ በቤንች ማጂ፣ በከፋ እና ጉራጌ ዞኖች በተመረጡ ትርፍ አምራች ወረዳዎች በተካሄዱ አሳታፊ የቴክኖሎጂ ሽግግር፤ የዝርያ መረጣና ማላመድ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም ምርምር በዋና ዋና ሰብሎች (በስንዴ፣ በብቅል ገብስ፣ በበቆሎ፣ በባቄላ እና በምግብ ገብስ) ምርትና ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ለመጨመር ማስቻሉን በወቅቱ ተገልጾአል፡፡

ከኔዘርላንድ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወነው የካስኬፕ ፕሮጀክት በፕሮጀክቱ ባለሞያዎች፣ በደቡብ ግብርና ምርምር ተቋምና በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ከክልል እስከ ቀበሌ ካለው መዋቅር ጋር በመቀናጀት አርሶ አደሮችና የኀብረት ስራ ማኀበራትን ከተለምዷዊ የግብርና ስራ ማላቀቅና በተግባራዊ ልምምድ የተደገፉ ስልጠናዎችን መስጠት ትኩረት የተደረገባቸው መስኮች መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሲዳማ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ሠለሞን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሀገራችን ገብስ በማምረት በአፍሪካ ከሚገኙ ሀገሮች ከሞሮኮ ቀጥሎ የ2ነት ደረጃ የምትይዝ ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የገብስ ዝርያዎችን በማምረት ቀደሚ መሆኗን ጠቁመው በፕሮጀክቱ በሚደረገው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ደጋማ አከባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የቢራ ገብስ በማምረትና ለፋብሪካዎች በማስረከብ የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው ምርቱን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

 

በፕሮጀክቱ ከታቀፉ አርሶ አደሮች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ከተመራማሪዎች ጋር ባከናወኗቸው ስራዎች የተሻሻሉ የእርሻ አሰራሮችን ከማወቃቸው በተጨማሪ በዕቅድ የመመራትና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመገምገም የተሻለውን ለመምረጥ፤ በሚሰጣቸው እገዛ መሠረት ሙሉ ፓኬጆችን በመጠቀም፤ አረምን በመቆጣጠርና በመስመር በመዝራት ውጤታማ መሆን እንዳስቻላቸው ገልፀው በአሁኑ ወቅት በተሰጣቸው ስልጠና ተጠቅመው በሄክታር 16 ኩንታል የነበረውን ምርት እስከ 54 ኩንታል ማድረስ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

                                                                                                          በዳዊት በዳሳ 

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.