የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም ከ7800 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ከ7800 በላይ ተማሪዎቹን ባለፉት ሰኔ 17፣ ሰኔ 24 እና ሰኔ 25 / 2009 ዓ.ም. በተለያዩ ካምፓሶች ባደረጋቸው የምረቃ በዓላት አስመረቀ፡፡
የመጀመሪያው ምረቃ ሰኔ 17/ 2009 ዓ.ም. የተካሄደው በወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ሲሆን በወቅቱ የኢፌዴሪ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ገመዶ ዳሌን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የኮሌጁ ማህበረሰብ ተገኝቷል፡፡ በወቅቱም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አያኖ በራሶ እንደገለጹት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመወጣት አንጻር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ከየዘርፉ አብነቶችን በማንሳት ገልጸዋል፡፡ ክቡር ዶ/ር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው በዕለቱ ተማሪዎች የተመረቁባቸው የተለያዩ ዘርፎች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ተልዕኮ ጋር በቅርብ የተቆራኙ በመሆናቸው ከሁሉም ተመራቂዎች ጋር በአንድም ሆነ በሌላ በኩል አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም የዘርፉን ስራ በተጨባጭ መስኩ ላይ ተገኝቶ ከመስራትና ውጤት ከማምጣት ጋር በተያያዘ ቀድሞ ይሰጥ የነበረው የዲፕሎማ መርሐ ግብር ዳግም የሚጀመርበት አግባብ ሊጠና እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ዜጋ የግልም ሆነ አገራዊ ራዕዩን እንዲያሳካ ሰላም የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ለሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያድርግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

በመቀጠልም የዋናው ግቢ፣ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የግብርና ኮሌጅ የዓመቱ ተመራቂዎች ሰኔ 24/2ዐዐ9 ዓ.ም. በዋናው ግቢ የተመረቁ ሲሆን አቶ አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በዕለቱ ተገኝተው የዩኒቨርስቲውን የበላይ ኃላፊዎችና መምህራኖች፣ ሰራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና ተመራቂዎችን የድካማችሁን ፍሬ ለማየት ስላበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
አቶ አያኖ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የመሆን ራዕይ አንግቦ በመስራት በስድስት ካምፖሶች በ81 የመጀመሪያ ድግሪ፣ በ1ዐ1 የሁለተኛ ድግሪ የህክምና እስፔሻሊቲን ጨምሮ እና በ16 የ3ኛ ድግሪ ፕሮግራሞች ከ38ዐዐዐ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በተከታታይ ትምህርት እያስተማረ መቆየቱንና በመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል በተካሄደው የአጠቃላይ አፈፃፀም ውድድር ለተከታታይ 4 ዓመታት ከ1ኛ-3ኛ ያሉ ደረጃዎችን መያዙን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱም ለዕለቱ ተመራቂዎች "ሀገራችን ከውስን ሀብቷ ውስጥ በርካታውን ለትምህርት በመመደብ የትምህርት እድል በሰፊው እንድታገኙ በማድረጓ እናንተም ያላችሁን ዕውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ለሀገራችን ህዳሴና እድገት እንድታበረክቱና እራሳችሁን ከመጥፎ ስነምግባርና ሙስና ድርጊቶች በማራቅ ለራሳችሁ፣ ለወላጆቻችሁና ለሀገራቸው አለኝታ በመሆን እንድትቆሙና በተመረቃችሁበት ሙያ ህዝባችሁን በቅንነት እንድታገለግሉ አደራ ለማለት እወዳለሁ" ብለዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ፕ/ር ይፍሩ ብርሃን የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር በኢፌዴሪ መንግስት እና በራሳቸው ስም እንኳን አደረሳችሁ በማለት ዕለቱን አስመልክተው የተሰማቸውን ደስታ የገለፁ ሲሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለመመረቅ መብቃታችሁ በራሱ አንድ ግብ ሆኖ በቀጣይ የሚጠበቅባችሁን ግላዊ ፍላጐትን ለማሳካትም ይሁን ሃገራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚኖራችሁ ቁርጠኝነትና በራስ መተማመን ዘላቂ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ እሴቶቻችሁ መሆናቸውን በመገንዘብ ነገን ዛሬ ለመስራት ተዘጋጁ ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ለተመራቂ ተማሪዎች እየተመረቃችሁ ያላችሁት መንግስት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት እየሰጠ ባለበት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የዓለምን ትኩረት በእጅጉ እየሳበች እና ተደማጭነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ስለሆነ ዕድለኞች ናቸሁ ያሉ ሲሆን ይህ የተማረ ሃይል በቀጣይ ለምናሳካቸው ግቦች ትልቁን ድርሻ እንደሚወሰድ በመተማመን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በአብዛኛው በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንደሆነ እና በተግባርም እየሆነ ያለው ይሄው ስለሆነ በምትሰማሩበት የስራ መስኮች ሁሉ ከሁሉ በፊት ስራን አስቀድሙ ሌላው እናንተ ሳታዩት እርሱ ይከተላችኋል ለማለት አሳስበዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በሰኔ 25/2ዐዐ9 ዓ.ም ባስመረቀበት ዕለት የተገኙት የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የደቡብ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት እያደረገ ላለው ውጤታማ ስራ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከተመስረተ አጭር ዕድሜ ያለው ቢሆንም በከፍተኛ ፍጥነት እያሳየ ያለውን ለውጥ አድንቀው የዕለቱን ተመራቂዎች መንግስት የልማት ማዕከላትን በጥናት በመለየት ለኢንደስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የኢንደስትሪ ፖርኮች ግንባታን በሰፊው እያካሄደ ባለበት ወቅት ለምረቃ በመብቃታችሁ ዕድለኞች ናችሁ ብለዋል፡፡
በምረቃዎቹ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ መስኮች ተመራቂያንም እንደገለጹት በየሰለጠኑባቸው መስኮች አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል እንዲሁም ብቃታቸውን በየጊዜው እያሻሻሉ ለመሄድ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡
By Sileshi Negash 

Newsletter

Make sure you dont miss interesting happenings by joining our newsletter program.

Contact us

Armaye Assefa
Director, Corporate Communication & Marketing Directorate

  • Phone: +251462200341/+251462209331/+251462212720

Connect with us

We're on Social Networks.
Follow us & get in touch.